Popular Posts

Friday, March 13, 2020

በተግዳሮት የተሸፈነ እድል


በድሮ ዘመን ነው አሉ፡፡ ከአሜሪካን ትልቅ የጫማ ኩባንያ ሁለት የሽያጭ ባለሙያዎች ወደ ቻይና ተላኩ፡፡
አንዱ ምን ዋጋ አለው የቻይና ሰዎች ጫማ የላቸውም፡፡ እዚህ አገር ጫማ መሸጥ አይቻልም ብሎ ተስፋ የመቁረጥ መልዕክት ይዞ ተመለሰ፡፡ ሌላኛው ግን ኧረ የሚገርም ነው የቻይና ሰዎች ጫማ የላቸውም፡፡ እባካቹ ብዙ ጫማዎች በፍጥነት ላኩ ብሎ እጅግ የተቃረነ መልክት ወደላከው የጫማ ኩባንያ ላከ፡፡
ልዩነታቸው አንዱ ተግዳሮቱን አይቶ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ሌላው ከተግዳሮቱ በስተጀርና ያለው እድል መመልከት ቻለ፡፡ ሁለቱ ሰዎች አንዱን ሁኔታ ያዩበት እይታ እጅግ ተቃራኒ ነበር፡፡ በዚህ ምክኒያት ሁለቱ ሰዎች አንዱን ሁኔታ የተረጎሙበት አተረጓጎም ተቃራኒ ነበር፡፡
እንዲሁም በመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ሙሴ ከላካቸው ሰላዮች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ነበሩ የሰለልናቸው ህዝቦች ታላላቆች ናቸው ግን እንደ እንጀራ ይሆኑልናል ያሉት፡፡ ሁለቱ የተባረኩ ሰላዮች ከጠላቶቻቸው ግዙፍነት በስተጀርባ ታላቅ ህዝብን የማሸነፍ እድልን አዩ፡፡ ሌሎቹ ሁሉ እኛ በእነርሱ ፊት ስንታይ እንደ አንበጣ ነን በማለት የተዛባ አስተያየታቸውን ሰጡ፡፡  
ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ። ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን፦ በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ። ኦሪት ዘኍልቍ 13፡30-31
ከማንኛውም ተግዳሮት በስተጀርባ የሚደንቅ እድል አለ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚደነቅ እድል ያለው ከተግዳሮት በስተጀርባ ነው፡፡
ጥያቄው ከተግዳሮት በስተጀርባ ያለውን እድል ማየት እንችላል ወይ ነው፡፡
ከተግዳሮቱ ባሻገር ማየት ከቻልን ተግዳሮቱን እንታገሰዋለን፡፡ ከተግዳሮቱ ባሻገር ማየት ካልቻልን ግን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡
እምነትም ያስፈለገው ከተግዳሮት ባሻገር እድልን ለማየት ነው፡፡ እምነት የሚታየውን ተግዳሮት አለማየት የማይታየውን የእግዚአብሄርን ቃል እድል ማየት ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡17-18
ከመከራ ተግዳሮት በስተጀርባ የክብር እድል አለ፡፡
በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡6-7
ከሃዘን ተግዳሮት በስተጀርባ የመፅናናትና የደስታ ታላቅ እድል አለ፡፡
የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። የማቴዎስ ወንጌል 5፡4
ከድካም ተግዳሮት በስተጀርባ የብርታት እድል አለ፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡9-10
ከነቀፋ ተግዳሮት በስተጀርባ የክብር መንፈስ እድል አለ፡፡
ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4፡14
ከተዘጋ የፈተና በር ተግዳሮት በስተጀርባ ሌላ የተከፈተ በር እድል አለ፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13
ከመዋረድ ተግዳሮት በስተጀርባ የክብር እድል አለ፡፡
የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡9-10
ከማጣት ተግዳሮት በስተጀርባ ፀጋን የማግኘት እድል አለ፡፡
ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡10
ከፈተና ተግዳሮት በስተጀርባ በሌላ በምንም መንገድ የማይገኝ የአክሊል እድል አለ፡፡
በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡12
ከድካም ተግዳሮት በስተጀርባ የመታደስ እድል እንዳለ ማወቃችን እንዳንታክት ያበረታናል፡፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡16
ካለመቻል፣ ካለመታወቅ ፣ ከሞት ፣ ከመቀጣት ፣ ከሃዘን ፣ ከድህነት እና ከማጣት በስተጀርባ አስደናቂ የመታወቅ ፣ የህያውነት ፣ የመቋቋም ፣ የደስታ ፣ የባለጠግነት እና የሙላት አስደናቂ እድል አለ፡፡
ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡9-10
ብዙ ጊዜ በህይወታችን ልዩነትን የሚያመጣው በህይወታችን የሚያጋጥመን ተግዳሮት ሳይሆን እኛ ተግዳሮቱን የምናይበት አስተያየት ነው፡፡ ተግዳሮቱን የምናይበት አስተያየት የሞትና የህይወት ያህል ልዩነት ያመጣል፡፡ ከተግዳሮቱ ባሻገር ያለውን እድል ካላየን ከተግዳሮቱ የተሻለን ነገር ማውጣት አንችልም፡፡  
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፈተና #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ጥበብ #ክፉ #አሸንፍ #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #እድል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ተግዳሮት #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ #ምስክርነት

No comments:

Post a Comment