Popular Posts

Thursday, March 12, 2020

እግዚአብሔር ይጨመርበት ብሎ ነገር



ሰዎች ስኬታማ ለመሆን እግዚአብሄር ለእነርሱ የተለየ የህይወት አላማ እና እቅድ እንዳለው ሊረዱ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ የህይወት አለማችንን እንድናዘጋጅ ከእኛ የፈጠራ ክህሎትን አይጠብቅብንም፡፡ እግዚአብሄር የራሱ ሃሳብ አለው፡፡ እግዚአብሄር የራሱ በቂ እቅድ አለው፡፡ ሰዎች እግዚአብሄር በህይወታቸው ያለውን እቅድ ፈልጎ በመከተል ብቻ ስኬታማ እንደሚሆኑ ብቻ ማስተዋል አለባቸው፡፡  
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11
አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት አድርገው ሲጨርሱ እግዚአብሄር ይጨመርበት ይላሉ፡፡ ሰዎች ሲጀመር ሳይፀልዩ የእግዚአብሄርን ሃሳብን ሳይፈለጉ የራሳቸውን መንገድ ጀምረው መንገድ ላይ እግዚአብሄር ወደሚሄዱበት ቦታ አብሮዋቸው መሄድ እንዳለበት ያስታውሳሉ፡፡
እግዚአብሄር አብሮን እንዲሄድ መፈለግ መልካም ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር አብሮን እንዲሄድ በመፈለግ ምንም የሚወጣለት እንከን የለም፡፡
ነገር ግን የእግዚአብሄርን መንገድ ፈልገን ከመከተል ይልቅው የራሳችንን መንገድ እየሄድን መጀመሪያ ያልፈለግነው እግዚአብሄር ሃይል ስንፈልግ ብቻ አብሮን እንዲወጣ መፈለግ ሞኝነት ነው፡፡
እግዚአብሄር የሚረዳው የራሱን እቅድ ነው፡፡ የራሱን እቅድ እንደ ባለቤት ይረዳዋል ይደግፈዋል፡፡ እግዚአብሄር የእኛን የግል ጥማትና ምኞት ስፖንሰር አያድርግም፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ፈልገን ከተከተለን እግዚአብሄር ይጨመርበት ሳንል እግዚአብሄር አብሮን ነው፡፡ ሲጀመር እግዚአብሄር ለእኔ ህይወት በቂ አላማ አለው ብለን ካሰብንና ያንን ልዩ አላማ ለመከተል ከወሰንን እግዚአብሄርን ፌርማታ መንገድ ላይ ማሳፈር እስከማያስፈልግን ድረስ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፡፡
ትዳራችንን መንፈሳዊ የሚያደርገው ሲጀመር በእግዚአብሄር ቃል መኖራችን እንጂ እግዚአብሄር የፈለገውን ሳይሆን እኛ የፈለግነውን ህይወት ኖረን በቤተክርስትያን ጣራ ስር ስልተጋባንና ሃይማኖታዊ ስርአት ስላደረግን አይደለም፡፡
እኛ ህይወታችን ክርስቶስ የሆንን ሰዎች እንጂ እግዚአብሄር ሰርተን ከጨረስን በኋላ ህይወታችንን እንዲያጣፍጥ እንደቅመም ጠብ የምናደርገው ነገር አይደለም፡፡
ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡4
እኛ ህይወታችን በዋጋ የተገዛ የራሳችን ያልሆንን ሰዎች እንጂ የህይወታችንን ትንሽ ክፍል ለጊዜው ለእግዚአብሄር የሚከራየው ሰዎች አይደለንም፡፡
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡19-20
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment