Popular Posts

Saturday, April 22, 2017

የአስተሳሰብ ንፅህና

ሰይጣን የሰው ልጅ ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን የሚመጣው ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ከመስረቅ ከማረድ እና ከማጥፋት ውጭ ሌላ ተልእኮ የለውም፡፡  
ሰይጣን በማይታዘዙት ልጆች ላይ የጥፋት አላማውን ይሰራል፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2
እኛ ግን ከጨለማው ስልጣን ስለዳንንና ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት ስለፈለስን በእኛ ላይ ስልጣን የለውም፡፡
እኛን የሚዋጋን በሃሳብ ነው፡፡ ሰይጣን ክፉ ሃሳብን ወደ አእምሮዋችን ይልካል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነውን ሃሳቡን ከተቀበልነው አላማውን ያስፈፅምብናል፡፡ ካልተቀበልነው ግን ሃሳቡና አላማው በውስጣችን ይሞታል፡፡
ሰው ሃሳቡ ከተበላሸ ህይወቱ ይበላሻል፡፡ ሰው በሃሳቡ የሃጢያትን ሃሳብ ካስተናገደ ሰው በህይወቱ የሃጢያትን ህይወት ያደርገዋል፡፡ ሰው ሃሳቡን ከሃጢያት ከጠበቀ ህይወቱን በንፅህና ይጨብቃል፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3
ሰው በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአብሄርን ከፈራ ከሃጢያት የነፃ ህይወት ይኖረዋል፡፡ ሰው አያየኝም ብሎ የሃጢያትን ሃሳብ የሚያስተናግድ ሰው ሃጢያትን ሲያደርገው ይገኛል፡፡
ሰው አስተሳሰቡ ቅጥ ያጣ መሆን የለበትም፡፡ ሰው አስተሳሰቡ ስርአት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ህይወታችንን በንፅህና ለመጠበቅ ማሰብ የሚገባን ነገሮች አሉ ማሰብ የማይገባን ነገሮች ደግሞ አሉ፡፡ ወደ አእምሮዋችን የመጣውን ሃሳብ ሁሉ አናስብም፡፡ በአእምሮዋችን ውስጥ እንዲቆይ የምንፈቅድለት ሃሳብ አለ፡፡ ከአእምሮዋችን በፍጥነት አሽቀንጥረን የምንጥለው ሃሳብ አለ፡፡
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
አእምሮዋችንን ከክፉ ሃሳብ ወረራ ከጠበቅን ህይወታችንን ከሰይጣን ጥቃት እንጠብቃለን፡፡
የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡5
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #ንፅህና #ምኞት #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት #ነፃነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, April 21, 2017

የፀሎት ልዩ መብት

ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ማቴዎስ 7፡7-8
መፅሃፍ ቅዱስ "መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው" (ዮሐንስ 1፡18) እንደሚል የእግዚአብሄርን ልብ የምናውቀው ከእግዚአብሄር ተልኮ በመጣው በኢየሱስ ንግግርና ትምህርት ነው፡፡
ኢየሱስ በምድር በተመላለሰበት ጊዜ ሰዎች ከእግዚአብሄር ፀልየው እንዲቀበሉ በተደጋጋሚ አስተምሮዋል አበረታቷል፡፡
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ሁሉን ቻይነትም ያውቀዋል፡፡
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ባለጠግነት ያውቀዋል፡፡
ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ ሮሜ 10፡12
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ደግሞ መልካምነት ፣ ርህራሄውንና ፈቃደኝነቱን ያውቀዋል፡፡
ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? ማቴዎስ 7፡9-11
የሰዎችን ሁኔታ ሲመለከት ከእግዚአብሄር ለምነው መቀበል ያለባቸ ብዙ ነገሮች እንዳለ በማየቱ የእግዚአብሄር ባለጠግነት ወደሰዎች በፀሎት አንዲተላለፍ በታላቅ ቅናት በተደጋጋሚ ስለ ፀሎት አስተምሮዋል፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። ዮሃንስ 16፡23-24
ኢየሱስ በእምነትም የሚለምን ሁሉ የሚለምንውን ነገር ሁሉ ከእግዚአብሄር እንደሚቀበል አስተምሮዋል፡፡  
አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው። ማቴዎስ 21፡22
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ማቴዎስ 77-8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፀሎት #አማርኛ #ለምኑ #ፈልጉ #መፅሃፍቅዱስ #አንኳኩ #መልካምእግዚአብሄር #ቃል #አእምሮ #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Thursday, April 20, 2017

የማያወላዳ የእምነት ምልክት

ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፦ በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች፦ ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ፦ ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ። ጌታም አለ፦ ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? ሉቃስ 188
የማይፀልይ ሰው የማይፀልየው ከእግዚአብሄር የሚፈልገው ነገር ስለሌለ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር የማይፈልገው ነገር የለም፡፡  የማይፀልይ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ሰው የማይፀልየው እግዚአብሄር ስለማያስፈልገው አይደለም፡፡ ሰው ምንም ነገር ባያስፈልገው እግዚአብሄር ያስፈልገዋል፡፡
ሰው ፀልዮ ከእግዚአብሄር የማይቀበለው ፀሎት እምነት ስለሚጠይቅ ነው፡፡ ሰው ባለጠጋ አባት እያለው በጉድለት የሚኖረው ለመፀለይ ሲሰንፍ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለምኑ ፀልዩ እያለ ደጋግሞ እያስተማረ ሰው ወደ እግዚአብሄር ፀልዮ የማይቀበለው ስለማያምን ነው፡፡
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ማቴዎስ 7፡7-8
የፀሎት መልስ ለትጉሆች እንጂ ለሰነፎች አይደለም፡፡ የፀሎት መልስ ለአማኞች እንጂ ለተጠራጣሪዎች አይደለም፡፡ የፀሎት መልስ  ለሚያቋርጡና ለሚረሱት ሳይሆን ሳያቋርጡ ለሚፀልዩ ነው፡፡
ጥያቄው እምነት አለ ወይ ነው፡፡ እምነት ካለ የፀሎት ጥያቄ ይመለሳል፡፡ ድል ሳያቋርጡ ለሚፀልዩ ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ማርቆስ 11፡22-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፀሎት #ፅናት #ትግስት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር

Wednesday, April 19, 2017

እኔም አሳርፋችኋለሁ ፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና። ማቴዎስ 11፡28-30
እግዚአብሄር ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአምስት ቀን ፈጠረ፡፡ እግዚአብሄር በሰባተኛው ቀን ከማረፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰውን በስድስተኛው ቀን ፈጠረው፡፡ ሰው የተፈጠረው እንዲያርፍ ነው፡፡ ሰው ዲዛይን የተደረገውና የተሰራው ለእረፍት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሰው ካላረፈ የሚጨነቀውና ፣ የሚጎሳቆለውና የሚታመመው፡፡ አለማረፍ ጤና አይደለም፡፡ አለማረፍ የነገሮች መዛባት ምልክት ነው፡፡
ኢየሱስም ወደምድር ሲመጣ ቃል የገነባው እረፍት ነው፡፡ ወደ ኢየሱስ በመምጣት ከነፍስ ጭንቀትና ከሰቆቃ ህይወት ማረፍ ይቻላል፡፡
ሰው የሚያርፈው በእግዚአብሄር ላይ ሲታመን ብቻ ነው፡፡ ሰው እንዳያርፍ የሚነዘንዙት ነገሮች ዙሪያውን ሳላሉ ሰው በእግዚአብሄር ላይ ካልተደገፈ አያርፍም፡፡  
ሰው ለማረፍ በእግአብሄር ላይ ቃል ላይ መታመን አለበት፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል የዋህ ያልሆነ የእግዚአብሄርን ቃል በሞኝነት የማይቀበል ሰው ሊያርፍ አይችልም፡፡ እግዚአብሄርን ለማመን የሚቸግረው ሰው ሊያርፍ አይችልም፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ የተናገረውን እንዳለ የማይቀበል ሰው ከእረፍት ይጎድላል፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡24-25
እግዚአብሄር በእርሱ ላይ ያለው አላማ ፍቅር መሆኑ ያልተረዳ ሰው ካለ እረፍት ዘመኑን ይፈጃል፡፡
ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ 2፡4
ለእናንተ የማስባትን ሃሳብ እኔ አውቃለሁና ያለውን እግዚአብሄርን በየዋህነት የማይቀበል ሰው ዘመኑ ይባክናል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
የሚያስጨንቃችሁን በእርሱ ላይ ጣሉት እርሱ ስለእናንተ ያስባልና ለሚለው ቃል የዋህ የማይሆን ሰው በዘመኑ ሊያርፍ በፍፁም አይችልም፡፡  
ሰው ትሁት ካልሆነ ለእግዚአበሄር አሰራት ጊዜል ካልሰጠ ሊያርፍ አይችልም፡፡  
ኢየሱስ የየዋህነትና የእረፍት ምሳሌ ነው፡፡ ኢየሱስ በአብ ተልኮ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ በምድር ላይ በአግዚአብሄር ፊት በሁሉ በሁሉ ትሁት ሆነ፡፡ ለእግዚአብሄር ሃሳብ ሁሉ የዋህ ሆነ፡፡ በእግዚአብሄር ስለታመነ በሁሉ እግዚአብሄርን ታዘዘ፡፡ እስከመስቀል ሞት ድረስ የታዘዘ ሆነ፡፡
ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ማቴዎስ 11፡29
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እረፍት #ቅድሚያ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ


Tuesday, April 18, 2017

የእግዚአብሄር መንግስት እንጂ ባለጠግነት ጉልበትህና ድካምህ አይገባውም

ለእግዚአብሄር ልጅ የገባውና የሚመጥነው ለእግዚአብሄር መንግስት መስራት ነው፡፡ የባለጠግነት ሩጫ ለእግዚአብሄር ልጅ አይገባም፡፡ ባለጠጋ ለመሆን መድከም ለእግዚአብሄር ልጅ የማይመጥነው ተራ ነገር ነው፡፡ ባለጠግነት ጉልበታችንና ድካማችን የማይገባው ተራ ነገር ነው፡፡
ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና። ምሳሌ 23፡3-5
 ኢየሱስ በምድር በተመላለሰበት ጊዜ  ለመብል ብለው የተከተሉትን ሰዎች ለእግዚአብሄር እንዲሰሩ አንጂ ለሚጠፋ መብል እንዳይሰሩ ያስተምራቸዋል፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንስ 6፡27
እጅግ ሃያል የሆነው የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን እንዳይሰራና ፍሬያማ እንዳንሆን የሚያደርገው የባለጠግነት ማታለል ነው፡፡
የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል።ሉቃስ 4፡19
ስለዚህ ነው ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ያለው፡፡ ለባለጠግነት መድከም ጌታን የማያውቁ የመንግስቱ አላማ የሌላቸው በኑሮ ከመካት የተሻለ አላማ በህይወታቸው የሌላቸው የተራ ሰዎች አካሄድ ነው፡፡
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው

ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዮሐንስ 3፡3-6
ኢየሱስ ኒቆዲሞስ ለተባለው የህግ መምህር ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሄርን መንግስት ሊያይ አይችልም አለው፡፡
ሰው ወደዚህ ምድር ለመግባት ከእናትና ከአባቱ መወለድ አለበት፡፡ ይህ መወለድ የመጀመሪያው መወለድ ነው፡፡ ስለዚህ መወለድ መፅሃፍ ቅዱስ በዮሃንስ 1፡13 ሲናገረው ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ በማለት ወደምድር መግቢያውን መንገድ ይናገራል፡፡
ወደዚህ ምድር ለመግባት በስጋ ከእናትና ከአባታችን እንደተወልድን ሁሉ መንፈስ ወደ ሆነው በአይን ወደማይታየው ወደ እግዚአብሄር መንግስት ለመግባት ደግሞ እንዲሁ መወለድ አለብን፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት በመንፈስ እንጂ በስጋ አይን ስለማትታይ በመካከላችን ብትሆንም ዳግመኛ ካልተወለድን ልናያት አንችልም፡፡
ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡20-21
ከእናትና ከአባታችን ባንወለድ ኖሮ ወደ ምድር መንግስት መግባት እንደማንችል ሁሉ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ካልተወለድን በስተቀር ወደ እግዚአብሄር /መንፈስ/ መንግስት መግባት አንችልም፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ዮሃንስ 4፡24
መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር የተወለደው መንፈስ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰው ከእናትና ከአባቱ ካልተወለደ የምድርን መንግስት ማየት እንደማይችል ሁሉ ሰው ደግሞ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ካልተወለደ የመንፈስን መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
መጀመሪያ ከእናትና ከአባቱ የተወለደ ሰው ሁለተኛ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሄርን መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
ከእናትና ከአባታችን የተወለድነውን የመጀመሪያውን መወለድ የስጋ መወለድ ይለዋል፡፡ ወይም ስጋችን ከስጋ እንደተወለደ ይናገራል፡፡ ከእናታችንና ከአባታችን የተወለደው ስጋችን ነው፡፡ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር የሚወለደው ደግሞ መንፈሳችን ነው፡፡
ሰው ከእናትና ከአባት ካልተወለደ በስተቀር ወደቤተሰብ መግባት እንደማይችል ሁሉ ሰው መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ካልተወለደ በስተቀር ወደእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ መግባት አይችልም፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ዮሃንስ 1፡12-13
ስለዚህ ነው ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር የተወለደው መንፈስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የተወለደ መንፈስ እንጂ ሌላ ምንም ነገር ሊሆን አይችልም፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #የእግዚአብሄርልጅ #ስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን

Sunday, April 16, 2017

የትንሳኤ በዓል በዓመት 365 ቀናት እንደሚከበር ያውቁ ኖሯል?

የትንሳኤ በአል በአመት አንዴ ከ365 ቀናት ውስጥ አንድ ቀን የሚከበር ከሆነ ከንቱ ነው፡፡ የትንሳኤ በአል መከበር ያለበት በህይወታችን ዘመን ሁሉ ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ በሁሉም የአመቱ ቀኖች መኖትር ይኖርብናል፡፡ ኢየሱስ የሞተበትንና የተነሳበትን አላማ በሁሉም የአመቱ ቀኖች ተጠቃሚ መሆን ይኖርብናል፡፡
ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ሞቷል፡፡ እኛ ደግሞ 365 ቀናት ለሃጢያት ልንሞት ይገባናል፡፡
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
ኢየሱስ በመሰቀል ላይ ተሰቅሎዋል እኛ ደግሞ 365 ቀናት ለአለምና ለምኞቱ መሞት ይገባናል፡፡
ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14
ኢየሱስ በሶስተኛው ቀን በድል ከሞት ተነስቷል፡፡ እኛም ለፅድቅ ህያው መሆን አለብን፡፡ ኢየሱስ በታላቅ ሃይል ከሙታን እንደተነሳ እኛም በመለኮራዊ ሃይል 365 ቀኖችን ለእግዚአብሄር መኖር ይገባናል፡፡
እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። ሮሜ 6፡11
ካልሆነ ግን በአመት አንድ ቀን ትንሳኤን ማክበት ከንቱ ነው፡፡ በአመት አንድ ቀን ብቻ ትንሳኤን ማክበር ኢየሱስ የሞተበትን አላማ መሳት ነው፡፡
መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡14
መልካም የትንሳኤ ህይወት!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ