Popular Posts

Monday, September 19, 2016

ድንበር ይከበር!

በክርስትና ህይወት ዘመኔ ድንበርን እንደማለፍና ልክን እንዳለማወቅ የክርስቲያንን ሰላም የሚረብሽ ነገር አላየሁም፡፡ ክርስትና የእግዚአብሄርና የሰው ድርሻ ያለበት ስራ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራው ነገር አለ፡፡ ሰው የሚሰራው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር የማይሰራው ነገር አለ፡፡ ሰው የማይሰራው ነገር ደግሞ አለ፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር አብረን የምንሰራ ነንና፡፡ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ህንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሰራ ነንና፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡9
ሰው ይህንን ሲረዳ መስራት ያለበትን ሰርቶ እርፍ ይላል፡፡ ሰው ግን ይህንን የስራ ክፍፍል ካልተረዳ የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት ሲሞክር ተስፋ ይቆርጣል ሰላሙንም ያጣል፡፡ ሰው ድርሻዬን ተወጥቻለሁ የሚልበት ደረጃ ከሌለ ጭንቀት ውስጥ ይገባል፡፡ ክርስትናውን ሊደሰትበት ያቅተዋል፡፡
  • ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከተረዳና ካደረገው በኋላ የእግዚአብሄርን ድርሻ መተው አለበት፡፡ የተስፋ ቃሉን መስጠት የእግዚአብሄር ስራ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካደረገ በኋላ ማረፍ ዘና ማለት አለበት፡፡ እግዚአብሄር ብቻ የሚፈፅመውን የተስፋ ቃሉን በራሱ ሊፈፅም መታገል የለበትም፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
  • ሰው የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ከፈለገ እግዚአብሄር ስለሚፈፅመው መብልና ልብስ መጨነቅ የለበትም፡፡ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ለክርስቲያን በቂ ሃላፊነት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን በመፈለግ ብቻ እርፍ ሊልና ደስ ሊሰኝ ይገባዋል፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
  • በህይወታችን ፅድቅን መራብና መጠማታችን በቂ ነው፡፡ የሚያጠግበው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ተርበንም እራሳችንን ለማጥገብም ከሞከርን ድንበር እያለፍን ስለሆነ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ማቴዎስ 5፡6
  • በመንፈሳዊ ህይወታችን ለማደግ ማድረግ የምንችለው ውስን ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ማጥናትና መታዘዝ ፣ ወደእግዚአብሄር መፀለይ ከቅዱሳን ጋር ህብረትን ማድረግ የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ሰው ግን ይህንን ካደረገ በኋላ ራሱን ሊያሳድግ በሚሞክረው ሙከራ ይረበሻል፡፡ የሚያሳድግ እግዚአብሄር ብቻ ነውና፡፡
እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡7
  • ሰው የዛሬን ሃላፊነቱን ከተወጣ ማረፍ ደስ መሰኘት የሰላም እንቅልፉን መተኛት አለበት፡፡ ሰው ግን የነገን ሃላፊነት ዛሬ ሊሰራው ሲሞክር ሰላሙን ያጣል፡፡ ህይወቱን ደስ ሊሰኝበት ያቅተዋል፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34
  • ሰው ክፋትን ሲሰራብን መቆጣት የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በቀልና ብድራትን መመለስ የእኛ ሃላፊነት አይደለም፡፡ ተቆጥተንም ብድራትንም ለመመለስ ስንሞክር ካለአቅማችን የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት እየሞከርን ነውና አይሳካልንም፡፡ እግዚአብሄርንም አይደሰትብንም፡፡ ነገር ግን ድርሻችንን አውቀን ለቁጣው ስፍራ መስጠት አለብን፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
  • ለክርስቲያን በኑሮም ሆነ በቃል ወንጌልን መስበክ የእለት ተእለት ስራው ነው፡፡ ነገር ግን ሰውን መለወጥ የሰው ስራ አይደለም፡፡ የሰው የወንጌል አገልግሎቱ የሚለካው በሚኖረው የህይወት ምስክርነትና በቃል የሚመሰክረው ምስክርነት ትጋት ብቻ እንጂ ጌታን በተቀበሉስ ሰዎች ብዛት አይደለም፡፡ የሚወቅስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
እርሱም (መንፈስ ቅዱስ) መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ዮሃንስ 16፡8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ንጉስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, September 18, 2016

ቀዳሚው ጥሪ

ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። ኤፌሶን 6፡5-9
ክርስትያን ስንሆን ጥሪያችን ሁሉ ሰማያዊ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ጥሪው በመጀመሪያ የክህነት አገልግሎት ነው፡፡ ዋናው ጥሪው ክህንነት ነው፡፡ ክርስቲያን ካህን ነጋዴ ፣ ካህን ሃኪም ፣ ካህን አስተማሪ ፣ ካህን ሹፌር ፣ ካህን ፀሃፊ ፣ ካህን ወታደር እንዲሆን ነው የተጠራው፡፡
ክርስቲያን ነጋዴ መሆኑን ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ አስተማሪ ማስተማሩን ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ ሃኪም ህክምናውንም ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ ካህን ማለት በእግዚአብሄርና በሰው መካከል የሚቆምና እግዚአብሄርን በማገልገል ሰውን የሚያገለግል ማለት ነው፡፡ ካህን እግዚአብሄርን ወክሎ በሰው ፊት ይቆማል፡፡ ካህን ሰውን ወክሎ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል፡፡ ካህን ስለሰው ለእግዚአብሄር የሚናገር እንዲሁም ስለ እግዚአብሄር ለሰው የሚናገርና የሚመሰክር ነው፡፡
በቤተሰብ ውስጥ ያለ ልጅ ልጅ ስለሆነ ብቻ አባቱ እንደሚንከባከበውና የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያሟላለት ልጅ ስለሆንን ብቻ ነው እግዚአብሄር የሚንከባከበን፡፡ እግዚአብሄር ስራን የሚሰጠን እኛን ለመንከባከብ ቸግሮት አይደለም፡፡ ስራን የሰጠን በዋነኝነት የክህንነት ስራችንን እንድንፈፅምበት ነው፡፡ እግዚአብሄር በየሙያ ዘርፉ የበተነን በእግዚአብሄር ልጅነት ባህሪ ተፅኖ እንድናመጣ ነው፡፡
እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 5፡14
እንደክርስቲያን ለአምልኮ በአንድ ላይ እንሰበሰባለን ከዚያም የመንፈሳዊ ህይወት ደረጃና እውነተኛውን መንገድ ለማሳየት ሰው ወደሚገኝበት ቦታ ሁሉ ወደ ክህንነት አገልግሎታችን እንበታተናለን፡፡
እግዚአብሄር ለምድር ጨውና የአለም ብርሃን እንድንሆን ነው እግረመንገዳችንን ስራን እንድንሰራ የፈለገው፡፡
እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ማቴዎስ 5፡15
ስራ የሰጠን ሰዎች መልካም ስራችንን አይትተው የሰማዩ አባታችንን እንዲያከብሩ የእርሱን ክብር ለሰዎች እንድናንፀባርቅ ነው፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
ለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ በገንዘብ የተገዙ ክርስትያን ባሪያዎችን እንኳን የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው በማለት ቀዳሚውና ዋነኛ ጥሪያቸው ክህንነት እንደሆነ የሚያስተምረው፡፡ ጥሪያችሁ ሰማያዊ ነው፡፡ የጠራችሁ እግዚአብሄር ነው፡፡ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው፡፡
ስራችሁ ሁሉ በቀዳሚነት አገልግሎት እንጂ የገንዘብ ማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ ገንዘብ የምታገኙት የክህነት አገልግሎታችሁን ስትሰሩ እግረመንገዳችሁን ስራውን ስለምትሰሩት ነው፡፡
ስለዚህ አገልግሎታችሁን ስትወጡ ለክህንነት አገልግሎት የጠራችሁን ጌታን እንጂ የምድር ጌቶቻችሁን እያያችሁ መሆን የለበትም፡፡ የምድር ጌታችሁ በማያይበት ጊዜ ሁሉ ለክህንነት የጠራችሁ ስለሚያያችሁ ለታይታ ብቻ አትስሩ፡፡ ስትሰሩ ለሰማዩ ጌታ እንደሚገባ በሙሉ ልባችሁ በትጋት ስሩ፡፡
ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ቆላስይስ 3፡22-23
የመጀመሪያ ጥሪያችሁ ሰማያዊ ቀዳሚው ሙያችሁ ክህንነት ስለሆነ ቀዳሚው ቀጣሪያችሁና ከፋያችሁ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ለምድር ጌቶቻችሁ ከልባችሁ ስትታዘዙ ስለክፍያ በፍፁም አታስቡ፡፡
ከፋያችሁ የቀጠራችሁ ለክህነት የጠራችሁ እርሱ ክርስቶስ ነው ፡፡
ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም። ቆላስይስ 3፡24-25
እግዚአብሄር ሲከፍል ደግሞ እንዴት እንደሚከፍል ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ነው የሚከፍላችሁ ማለት ክፍያችሁ በሰማያዊ ምንዛሪ ነው ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች እኔ የራሴን ስራ ነው የምሰራው ማንን ነው ማገልገል ያለብኝ የሚል ይኖራል፡፡
አንተ ደግሞ የምታገለግለው አገልግሎት የምትሰጠውን የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የንግድ ድርጅት ካለህ የምድር ጌቶችህ ካንተ የሚገዙና ላንተ የሚሸጡ በንግድ ለምትገኘው ማንኛውም ሰው ሁሉ የጌታን መልካምነት ማሳየትና በቅንነት ልታገለግላቸው ይጠበቅብሃል፡፡
ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ቆላስይስ 3፡23
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ክህንነት #ምስክር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ኢየሱስ ጌታ ነው

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ጌታ ነው በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው በሚለው የሶስት ቃላት አረፍተ ነገር ውስጥ እጅግ የተጠቀጠቁ ትርጉሞች ይገኙበታል፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ሲባል
1. ኢየሱስ በሰማይ በምድር ከምድር በታች ሃያል ነው ማለት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡9-11
2. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞቱ የሻረ ብቸኛ የነገስታት ንጉስ ነው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ እስኪመጣ ድርስ ሞት ሃያል ጌታ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሞትን ያሸነፈ ማንም አልነበረም፡፡ ኢየሱስ ሲመጣ ግን በሞት ላይ ስልጣን ያለውን ሰይጣንን በሞቱ መሻሩን ያሳያል፡፡
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ ዕብራውያን 2፡14-15
3. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ሃይላትንና ስልጣናትን የገፈፈ የመጨረሻው ባለስልጣን ነው ማለት ነው ፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ኤፌሶን 1፡20-21
4. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ላይ መሪና ወሳኝ ነው ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በልባችን የመጀመሪያው ስፍራ የእርሱ ነው ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ከእርሱ ጋር የምናወዳድረው ምንም ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡ በልባችን ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ ነው ማለታችን ነው፡፡
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡15 ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል እርሱን ከሁሉም በላይ እንወደዋለን ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል ከእርሱ ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡38-39
5. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል ከእጁ የሚነጥቀን ማንም ሃይል የለም በማለት እየተመካን ነው፡፡ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። ዮሐንስ 10፡29
6. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ላይ ጌታ ሊሆን የሚችለውን ነገር ሁሉ ላይ ጌታ ነው ማለታችን ነው፡፡
ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡38፣37
7. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት የዳነው በኢየሱስ ጌትነት ነው ማለታችን ነው፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10
8. የምንሰብከው እንኳን ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን።
9. በቃልም ሆነ በስራ የምናደርገውን ሁሉ በጌታ ኢየሱስ ስም የምናደርገው ስለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ቆላስይስ 3፡17
10. በመጨረሻም የምንነግሰው የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ነው፡፡
እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ። ራእይ 7፡14 ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ንጉስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, September 17, 2016

ፈንታ አትስጡት!

የሰይጣን ዲያቢሎስ ብቸኛ አላማ መስረቅ ማረድ እና ማጥፋት ነው፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ከእነዚህ ውጭ ምንም አይነት አላማ የለውም፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሐንስ ወንጌል 10፡10
እየሱስ ደግሞ የመጣው ህይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም ነው፡፡ እንግዲህ በህይወታችን ስፍራ የምንሰጠው አለማውን ይፈፅማል፡፡ ስለዚህ ነው ለዲያቢሎስ ስፍራን አትስጡት ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስጠነቅቀው፡፡ ለዲያቢሎስ ስፍራን ከሰጠነው የመስረቅ የማረድና የማጥፋት አላማውን በእኛ ላይ ይፈፅማል፡፡
ሰይጣን በህይወታችን ከሰረቀ ካረደና ካጠፋ ስፍራን ሰጥተነዋል ማለት ነው፡፡ እኛ ስፍራን ካልሰጠነው ሊሰርቀን ሊያርድና ሊያጠፋ የማይችል የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀሉ ስራ ሰይጣንን ፈፅሞ ስላሸነፈው ካልፈቀድንለትና በህይወታችን ስፍራ ካልሰጠነው በስተቀር በሃይል ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ሰው አንዴ ለዲያቢሎስ ስፍራ ከሰጠው ስራውን እየጨመረ ህይወትን መስረቅ ማረድና ማጥፋቱን እያበዛውና ፈፅሞ እስከሚያጠፋ ድርስ እያስፋፋው ይሄዳል፡፡ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27 ለዲያቢሎስ ስፍራ የምንሰጥበት መንገዶች ምንድናቸው
  • ቁጣን አለመቆጣጠር ፣ ይቅር አለማለትና ምሬት
መቆጣት አግባብ ነው፡፡ ነገር ግን ከልክ ሲያልፍ ምሬት ይሆናል፡፡ ቶሎ ይቅር ካላልን በስተቀር በህይወታችን ለዲያቢሎስ ስፍራን እንሰጠዋለን፡፡
ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ኤፌሶን 4፡26-27
የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ አይሰራም፡፡ የሰው ቁጣ መጠኑ ስለማይታወቅ አደገኛ ነው፡፡ የሰው ቁጣ ጥበብ ስለሚጎድለው የቁጣን ትክክለኛ አላማ ግቡን እንዲመታ አያደርገውም፡፡ የሰው ቁጣ የራስን ስሜት ከመግለፅ ውጭ አለምን በፅድቅ የማስተዳደር አቅም የለውም፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን ፣ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሰራምና" ይላል ። ያዕቆብ 1 : 19 – 20
ስለዚህ ነው ሁልጊዜ ለእግዚአብሄር አገዛዝ ስፍራ መስጠት ያለብንና ራሳችን መበቀል የሌለብን፡፡ አለምን የምንመራው እግዚአብሄር እንጂ እኛ ስላይደለን ከሰው ጋር ስንጣላ የሁለታችንም ጌታ በሰማይ አንዳለ እውቅና መስጠት አለብን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
  • ጥላቻ
በህይወት ዘመናችን የምንጠላው ዲያቢሎስን ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ አንዱንም የእግዚአብሄር ፍጥረት እንድንጠላ ፈቃድ የለንም፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን በርን የምንከፍትበት መንገድ ነው፡፡ ጥላቻ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ሰይጣን በጥላቻ ልብ ውስጥ ዘርቶት የማይበቅልለት የመስረቅ የማረድና የማጥፋት ዘር የለም፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን ምቹ ቦታ ነው፡፡ ጥላቻ በሌለበት ልብ ውስጥ ሰይጣን መስራት አይችልም፡፡ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 1ኛ ዮሐንስ 3፡14-15
  • ትእቢት
ሌላው ኢየሱስ ሰይጣንን አሸንፎት ሳለ ሰይጣን ህይወታችንን የሚሰርቅበት የሚያርድና የሚያጠፋበት መንገድ በትእቢት ለሰይጣን ስፍራ መስጠት ነው፡፡ ትእቢት ከሆኑት በላይ ራስን ከፍ አድርጎ ማየት ነው፡፡ ትእቢት እግዚአብሄር ያልሰጠቅውን ደረጃ መውሰድ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
ትእቢት ሁሉንም ከእግዚአብሄር ተቀብለነው ሳለ የእኛ እንደሆነ ምንጩ እኛ ራሳችን እንደሆንን ማሰብ ነው፡፡
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
ሰይጣንን የምንቃወመው በእግዚአብሄር ፀጋ ሲሆን እግዚአብሄር ደግሞ ፀጋን የሚሰጠው ለትሁታን ብቻ ነው፡፡ ለትእቢተኛ ፀጋን አይሰጥም፡፡ እንዲያውም ትእቢተኛን ይቃወመዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ተቃውሞ የሚቋቋሞ ማንም የለም፡፡
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። ያዕቆብ 4፡6
ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት! ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Thursday, September 15, 2016

አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥

ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ማቴዎስ 5፡8
ስለዚህ ነው እግዚአብሄር እንደልቤ ያለው ዳዊት ይህንን ፀሎት የሚፀልየው፡፡ ልባችንን ሊያቆሽሽ የሚመጣ ነገር ባለበት የፃም የልብ ጩኸት የልብ ንፅህና ነው፡፡
አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። መዝሙር 51፡10
ልበ ንጹሖች እግዚአብሄርን ያዩታል፡፡ በስራቸው እግዚአብሔርን ያዩታል በህይወታቸው የእግዚአብሄር ክንድ ያያሉ፡፡ በኑሮዋቸው የእግዚአብሔርን ሃይል ያያሉ፡፡ በአካሄዳቸው የእግዚአብሔርን ክንድ ያዩታል፡፡ በዘመናቸው እግዚአብሔርን በስራ ላይ ያዩታል፡፡ ልበ ንጹሖች እግዚአብሔር ሲዋጋላቸው ያዩታል፡፡
እግዚአብሔር ንፁህና ቅዱስ ነው፡፡ ካለቅድስና እግዚአብሄርን ማየት አይቻልም፡፡ እግዚአብሄር ይኖራል ይሰራልም፡፡
እግዚአብሄርን በህይወታችን ለማየት ግን የልብ ንፅህናን ይጠይቃል፡፡ የልብ ንፅህና ምንድነው? የልብ ንፅህና ከምኞት መንፃት ነው፡፡ ሰዎች በምኞት ልባቸው ቆሽሾ እግዚአብሔን ማየት በፍፁም አይችሉ፡፡
  • ከጥላቻ የነፃ ልብ
ሰዎች እንደ እነርሱ እግዚአብሄር የፈጠረውን ሰው ሲጠሉ እግዚአብሄር ሲሰራ ማየት ይሳናቸዋል፡፡
ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 4፡8፣16
  • ከራስ ወዳድነት የነፃ ልብ
ሰዎች በራስ ወዳድነት ሲመላለሱ የእግዚአብሄር መኖርም ይሁን የእግዚአብሄር ስራ ይጨልምባቸዋል፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1-3
  • ከክፋትና ከቅናት የነፃ ልብ
በሰው ላይ ክፉ በማድረግ ከመርካት ልባችንን ልናጠራ ይገባናል፡፡ የሰው ውድቀትና አለመከናወን የሚያስደስተን ከሆንን እግዚአብሄርን ልናየው አንችልም፡፡
እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ያዕቆብ 4፡8
  • ከስስት የነፃ ልብ ከስስት ነፃ መሆን፡፡ ያለኝ ይበቃኛል አለማለት፡፡ እግዚአብሄር ከሚባርከን ከመሰረታዊ ፍላጎት በላይ አለመመኘት፡፡
ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል፡፡ ሉቃስ 11፡39
  • በሁለት ሃሳብ የማይወላውል ልብ እግዚአብሄርን የመጀመሪያ ማድረግ፡፡ እግዚአብሄርን ባጣ ቆየኝ አለማድረግ፡፡ በእግዚአብሄር ማመን፡፡ በእግዚአብሄር ብቻ መርካት፡፡ እግዚአብሄርን አለመጠራጠር፡፡
ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ያዕቆብ 4፡8
ልብን የሚያጠራው ብቸኛ መፍትሄ የእግዚአብሄን ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የእግዚአብሄርን ቃል በተረዳንና በታዘዝነው መጠን ልባችንን ያነፃዋል፡፡ ልባችን በነፃ መጠን አግዚአብሄርን በአብሮነቱ እናየዋለን፡፡
እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ ዮሐንስ 15፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#እግዚአብሔር #አምላክ #ፍቅር #እምነት #ልብ #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ