Popular Posts

Thursday, June 16, 2016

የክርስትናችን ማተብ

ክርስትና የህይወት ጉዳይ ነው፡፡ ክርስትና ለሞተልን ለእየሱስ እና ለእርሱ ብቻ መኖር ነው፡፡ ታዲያ የአማኝ ክርስቲያን ምልክቱ ምንድነው? ክርስቲያን ክርስቲያንነቱ በምን ይታወቃል? አንድን ክርስቲያን በስም ብቻ ሳይሆን በእውነት ክርስቲያን የሚያደርገው ምንድነው?
ይህ ጥያቄ በህይወታችን ቸል ልንለው የማይገባ ነገር ግን በሚገባ ከልባችን ልንመልሰው የሚገባን ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ወሳኝ ጥያቄ በሚገባ መመለሳችን ህይወታችንን በከንቱ እንዳንሮጥ ይጠብቀናል፡፡
የአማኝነት ምልክት ምንድነው? የክርስቲያንነታችን እውነተኛ መለያ ምንድነው?
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡5-8
የክርስትናችን ምልክት እምነታችን ነው፡፡ ክርስትናችን በልብሳችን ክርስትናችን አንገታችን ላይ በምናደርገው ምልክት ምልክት አይታወቅም፡፡
የክርስትና እምነታችን ደግሞ የሚታየው በአኗኗራችን ነው፡፡ የአማኝ ክርስቲያን ምልክቱ ለጊዜው በምድር ላይ ሲኖር ወደ መንግስተ ሰማያት እሰከሚሄድ ድረስ ከጌታ እየሱስ ተለይቶ በስደተኝነት እንደሚኖር ማወቁ ነው፡፡ የአማኝ ምልክቱ የስደተኛ ኑሮ ነው፡፡
ሰው ግን በምድር ላይ ሲኖር የሚፈራው አምላክ እንደሌለው እንደ ልቡ በራሱ ላይ ራሱ ጌታ ሆኖ በራሱ መንገድ የሚኖር ከሆነ የአማኝነት ማተብ የለውም፡፡
ሰው ግን በምድር ላይ ሲኖር ዛሬ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡32) በሚል አስተሳሰብ የሚኖር ከሆነ አማኝ አይደለም፡፡
ሰው ግን በምድር ሲሆን እንደ እንግዳና መጻተኛ የማይኖርና በአለም ክፉ ውድድር ውስጥ ገብቶ በአለም ስጋዊ ምኞት የሚኖር ከሆነ አልታመነም፡፡
ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡11
ሰው ግን በምድር ሲኖር ምድር ጊዜያዊ ብቻ መኖሪያው እንደሆነ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚሄድ በእግዚአብሄር ፊት እንደሚቀርብና እንደሚጠየቅ አድርጎ እግዚአብሄርን በመፍራት ካልኖረ የክርስትና ማተብ የለውም፡፡
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ፊልጵስዩስ 3፡19-20
መፅሃፍ ቅዱስ በእምነታቸው ስለተመሰከረላቸው ስለእምነት አባቶች ሲናገር በዕብራዊያን መፅሃፍ ላይ እንዲህ ይለናል፡፡
እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። ዕብራውያን 11፡13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum...

Wednesday, June 15, 2016

ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል

እግዚአብሄር ታላቅ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ታዕምራትን የሚያደርገው ብቻውን ነው ፡፡ አሁን ያለንበት ደረጃ ከጥቂት አመታት በፊት ተራራ የነበረብን የክርስትናና የአገልግሎት ደረጃ ነው፡፡ አሁን ግን ደርሰንበታል እየኖርነው ነው፡፡ አሁን የምናስባቸው ተራራ የሆኑብን ነገሮች ደግሞ እንዲሁ በእግዚአብሄር ይደረስባቸዋል፡፡

የእስራኤል ህዝብ በጦርነት ላይ በነበረ ጊዜ በምድረበዳ ለራሳቸውና ለከብቶቻቸው የሚጠጡት ባለማግኘታቸው በህይወታቸው እጅግ ተጨንቀው ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡፡

እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 1 ነገስት 3፡17

እግዚአብሄር በታእምራት ሊያኖረን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ታእምራትን ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ ደግሞም ለእግዚአብሄር ታእምራትን ማድረግ ድንቅ አይደለም፡፡

ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ 1 ነገስት 3፡18

እግዚአብሄር ታዕምራትን ለማድርግ እጅግ መዘጋጀትና ብዙ ምልክቶችን ማድርግ አይጠበቅበትም፡፡ ምልክቶች እንኳን ባይኖሩም እግዚአብሄር ከመቀፅበት ታዕምርን ለማድረግ ይችላል፡፡

ግን ሁሌ የእኛን ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ጌታ እንዲያውም ጊዜ የሚወስድው እኛን በማዘጋጀት ስራ ላይ ነው እንጂ ታዕምር የማድርግ ስራ ላይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የእስራኤል ህዝቡ አስቀድሞ እንዲዘጋጁ እግዚአብሄር በነቢዩ እንዲህ አለ፡፡

እንዲህም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፍሩ። 1 ነገስት 3፡16

ለምን ? ታዕምራቱ ሲመጣ ውሃው ሲመጣ ውሃውን መያዣ ጉድጉዋድ ከሌለ ታዕምራቱ ለታቀደለት ጊዜ ሊቆይና በታቀደለት አላማ ላይ ሊውል አይችልም፡፡ የእኛ ዋናው ድርሻ ተአምራቱን ማቆየትና የተአምራቱን ውጤት ለረጅም ጊዜ የመጠቀም ሃላፊነት ነው፡፡

ይህ የእግዚአብሄር ሃላፊነት በፍፁም አይደለም፡፡ ይህን ታእምራቱን አቆይቶ ለታለመለት አላማ ማዋል የሰው ድርሻ ነው፡፡ ስለዚህ የታዕምራቱን መምጣት ስንጠብቅ በትጋት እንዘጋጅ፡፡
የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ምሳሌ 16:1

Abiy Wakuma Dinsa
#amharic #ethiopia #spiritual #christian #jesus 

Tuesday, June 14, 2016

የሚመለስ ፀሎት

መፀለይ እጅግ መታደል ነው፡፡ ይህን ታላቅ እድል በአግባቡ መጠቀም በህይወታችን ፍሬያማ እንድንሆን ያደርጋል፡፡
ፀሎት ሲባል አብዛኞቻችን ወደ ሃሳባችን የሚመጣው ለእግዚአብሄር መናገር ነው፡፡ ይህ አመለካከታችን እግዚአብሄር በፀሎት ውስጥ ያስቀመጠውን ሙሉ በረከት ተጠቃሚ እንዳንሆን ያደርጋል፡፡
ፀሎት መናገርን ይጨምራል እንጂ ፀሎት መናገር ብቻ አይደለም፡፡ ፀሎት እግዚአብሄርን መስማትና ለእግዚአብሄር መናገር ነው፡፡ ልብ አድርጉ ፀሎት ለእግዚአብሄር መናገርና እግዚአብሄርን መስማት ነው አላልኩም፡፡ፀሎት ከእግዚአብሄር መስማትና ለእግዚአብሄር መናገር ነው፡፡
በፀሎት እግዚአብሄርን መስማት ይቀድማል፡፡
እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። መክብብ 5፡2
አንደኛ ወደ እግዚአብሄ ስትመጣ ለመስማት ተዘጋጅተህ ና እንጂ ለመናገር አትቸኩል፡፡
ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ መክብብ 5፡1
በፀሎት መስማት ቀዳሚ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የፀሎት ዋናው ክፍል መስማት መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ምክኒያቱም እንዴት እንድንፀልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነው፡፡
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንፀልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ሮሜ 8፡26
ፀሎት በአቦ ሰጥ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ እንደው የራሳችንን የግል ሃሳብ እንደመጣልን አነብንበን ሄደን ከእግዚአብሄር መልስ መጠበቅ አንችልም፡፡
ፀሎታችን እንዲመለስ ከፈለግን መንፈስ ቅዱስ ያለማወቅ ድካማችንን እንዲያግዝ ለመንፈስ ቅዱስ ጊዜ መስጠትና መንፈሱን እንዲያመለክተን መጠበቅ አለብን፡፡ መንፈሱን በልባችን መፈለግ መጠበቅና መስማት አለብን፡፡
የፀሎት ቀዳሚውና ዋናው ክፍል መንፈሱን መስማት ነው፡፡
አንዴ መንፈሱ ለጊዜው ለእኛ ያለውን ፈቃድ ካወቅን ብቻ ነው ያንን ለእግዚአብሄር መናገር የሚገባን፡፡ ስለዚህ ነው የፀሎት ዋናው ክፍል መስማት ነው የሚባለው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum/notes

Sunday, June 12, 2016

ፍርድ ሲዛባ


ብዙ ጊዜ ሳናውቀው ጥሩ የሰራን እየመሰለን የሚያስፈርድብንን ነገር ስናደርግ እንገኛለን፡፡ አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም ይላል እየሱስ ሲያስተምር፡፡

አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ። ሉቃስ 6፡36-37

·         የፍርድ ችግሩ ፈራጁ ራሱ ህጉን አይጠብቅም፡፡ የፈሪሳዊያን ችግር ለመፍረድና ለመቅጣት ፈጣን ናቸው፡፡ እነርሱ ግን በተመሳሳይ በደል ውስጥ የሚኖሩ ግብዞች ናቸው፡፡

ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ማቴዎስ 23፡2-4

·         የመፍረድ ስህተቱ ሰው በሚሰፍርበት በዚያው መስፈሪያ ቢሰፈርለት ለእርሱ ይጎዳዋል እንጂ አይጠቅመውም፡፡

እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። ማቴዎስ 7፡1-2

·         የመፍረድ ችግሩ የቤተሰብነት ስሜት ከማጣት የሚመነጭ ስለሆነ ነው፡፡ የሚፈርድ ሰው የራሱን ገመና ከመሸፈን ይልቅ የሚያማው የራሱን ቤተሰብ አባል ነው፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? ያዕቆብ 4፡11-12

·         የሚፈርድ ሰው ሌሎች ህጉን እንዲጠብቁ እንደሚረዳ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ሰዎች ህጉን እንዲፈፅሙ ምንም የሚያደርገው አስተዋፅኦ ስለሌለ የሚፈርድ ሰው ህጉን እንደሚያማ ይቆጠራል፡፡ የሚፈርድ ህጉ ሊፈፀም የማይችል ከባድ ነገር እንደሆነ ነው የሚያመለክተው እንጂ ሰው ህጉ እንዲፈፅም የሚያበረክተው ምንም አስተዋፅኦ የለም፡፡

 
በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ ያዕቆብ 4፡11

·         የሚፈርድ ሰው እራሱ ደግሞ እንደሚፈረድበት ሰው ትሁት ያላደረገ ነገር ግን በፈራጅ ቦታ የተቀመጠና አብሮት የሚፈረድበት ሰው ላይ በክፉ ሃሳብ ሊፈርድ የሚሞክር ትምክተኛ ነው፡፡ በክፉ ሃሳብ የምንፈርድ ሰዎች አንሁን፡፡ ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን?ያዕቆብ 2፡4
 

ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? ያዕቆብ 4፡12

አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤

 

Saturday, June 11, 2016

የህይወት መንፈስ

እየሱስን አዳኛችን እና የህይወታችን ጌታ አድርገን ከተቀበልነው ቅፅበት ጀምሮ እየሱስ በእኛ ውስጥ መኖር ይጀምራል፡፡
እየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ በእግዚአብሄር አብ እየተመራ እግዚአብሄርን አስደስቶታል፡፡ አሁንም እየሱስ በውስጣችን የሚኖረው እርሱ በምድር ቆይታው እግዚአብሄርን ደስ እንዳሰኘ እኛም እንዴት እግዚአብሄርን ደስ እንደምናሰኝ ሊያስተምረን ሊመራን ነው፡፡
በውስጣችን መለኮታዊ ህይወት አለ፡፡ በውስጣችን እየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ይኖራል፡፡
በውስጣችን ያለውን እየሱስን በሚገባ ከተከተልን እግአብሄርን በኑሮዋችን ማስደሰት እንችላለን፡፡
እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡27
እግዚአብሄር ከእኛ የሚፈልገው በራሳችን አነሳሽነት ይህን ይፈልጋል እያልን እየገመትን እንድኖር በፍፁም አይደለም፡፡ ወይም ክፉና ደጉን እንደምታሳውቀው ዛፍ አትቅመስና አትንካ በሚሉ ትእዛዞች እንድኖር አይደለም፡፡
ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ቆላስይስ 2፡20-22
በውስጣችን ያለው የእግዚአብሄር ህየወት አንድን ነገር ለማድረግ ሲነሳሳ አብረነው ካደረግን በውስጣችን ያለው ህይወት አይሆንም እንቢ ሲለን ካቆምን በውስጣችን ያለው ህይወት ቆይ ጠብቅ ሲለን ከጠበቅን ልባችንን በመከተል እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት እንችላለን፡፡
እግዚአብሄር ሁል ጊዜ ይመራናል፡፡ ልጆች እርግጠኛ ካልሆኑ የአባታቸውን ፊት እንደሚያዩት እኛም በአስተሳሰባችን በንግግራችንና በድርጊታችን የእግዚአብሄርን የፈገግታ ፊትና የመኮሳተር ፊት በልባችን ውስጥ ልንፈልግ ይገባናል፡፡
በውስጣችን ያለውን ህይወት ከተከተልን እግዚአብሄርን እንደምናስደስት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲያውም ውስጣችንን ከመከተል የበለጠ እግዚአብሄርን ማስደሰቻ ሌላ አስተማማኝ መንገድ የለም፡፡
ውስጣችንን ካልተከተልን ግን ምንም ያህል ያወቅን ቢመስለንና ሰውኛ ምክኒያቶች ቢኖሩን ከእግዚአብሄር ጋር እንተላለፋለን፡፡

Friday, June 10, 2016

መዝሙርን ዘፈን ያላደረገው


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘፈን ሃጢያት ነው ? የሚል ጥያቄ ተነስቶ ብዙዋቻችንን ሲያነጋግር ቆይቶዋል፡፡ እኔም በልቤ ያለውን የሚሰማኝን ዘፈን ሃጢያት ነው በሚል ርእስ ፅሁፍን ፅፌ ነበር፡፡
እግዚአብሄር መዝሙርን እንደሚፈልግ ዘፈንን ግን እንደማይፈልግ እንዲያውም ዘፋኝነት የስጋ ስራ እንደሆነ እነዚህን የሚያደርጉም የእግዚአብሄርን መንግስት እንደማይወርሱ መፅሃፍ ስለዘፈን ጎጂነትር በአፅንኦት ይናገራል፡፡
እግዚአብሄር ዘፈንን ለምን ጠላ መዝሙርንስ ለምን ወደደ? የሚለውን ለመመለስ መዝሙር ከዘፈን የሚለይበትን ነገሮች ማወቅ ግድ ይላል፡፡ መዝሙር እንደ ማንኛውም ዘፈን በግጥም በዜማ የሚሆን እንጉርጉሮ ቢሆንም እንዲሁም መዝሙርንም ዘፈንም የምንጫወትበት መሳሪያ ተመሳሳይ ቢሆንም መዝሙርን ዘፈን የማያደርገው ብዙ ወሳኝ መሰረታዊ ነገሮች አሉት፡፡
መዝሙርን ዘፈን ያላደረገው
1. የመዝሙር አላማ ሰዎች በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠሩ ክቡራን እንደሆኑና ሰይጣንን ሰምተው በሃጢያት እንዳይዋረዱና ከንቱ እንዳይሆኑ እግዚአብሄር እንደ ፈጠራቸው የክብር ደረጃ እንዲኖሩና ማስተማር ነው፡፡

2. የመዝሙር አላማ ሰዎች እግዚአብሄር በክርስቶስ የከፈለላቸውን የሃጢያት ዋጋ እንዲረዱና ክርስቶስ ለእነርሱ እንደሞተላቸው እነርሱ ደግሞ ለሃጢያት ሞተው ለክርስቶስ እንዲኖሩ የሚያበረታታ ነው፡፡
3. የመዝሙር አላማ ሰዎች የህይወት ጠላት የሆነውን ዲያቢሎስን እና ስራውን ከህይወታቸው እንዲክዱ ልቅነትንና ሃጢያትን እንዲፀየፉ ራስን እንዲገዙ ማበረታታት ነው፡፡
4. የመዝሙር አላማ ሰዎች በጊዜያዊ የአለም ደስታ ዘላለማዊ ህይወታቸውን እንዳያጡ የዘላለም ህይወታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ለማበረታታት የታለመ ነው፡፡
5. የመዝሙር አላማ ሰዎች በምድር ላይ ጊዜያዊ ተላላፊ ምፅአተኛ እንደሆኑ አውቀው በአለም ጉድፍ ራሳቸውን እንዲጠብቁ መምከር ነው፡፡
ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤1ኛ ጴጥሮስ 2፡11 
6. መዝሙር ሰዎች ለፈጠራቸው ባለቤታቸው ለሆነውና ዘወትር ክብር ለሚገባው ለእግዚአብሄር ክብር እንዲሰጡ የሚመራ ነው፡፡
7. መዝሙር እግዚአብሄርን ከምንም በላይ እንዲያከብሩና እርሱን ለማስደሰት እንዲኖሩ የስጋ ምኞታቸውንና የነፍሳቸውን ክፉ ፍላጎት እንቢ እንዲሉ እግዚአብሄርን ለማሳየት የሚዘመር ነው፡፡
8. መዝሙር እንካ በእንካ ያልሆነን ከራስ ወዳድነት የፀዳ ልጁን እየሱስን ለእኛ በመስጠት ያሳየውን የእግዚአብሄርን እውነተኛ ፍቅር የሚገልፅ ነው፡፡
9. እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ለእግዚአብሄር አምላክነት ስንገዛና እግዚአብሄ የፈጠረንን አላማ ስንከተል ብቻ እንጂ በተለያየ ቁሳቁስና ልምምድ የማይመጣ መሆኑን የሚያሳይ መዝሙር ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

መንግስትን ሊሰጣችሁ

አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ሉቃስ 12፡32

በህይወት በጣም የምንጨነቅባቸውና ብዙውን ጊዜያችንን እንድናጠፋባቸው የምንፈተንባቸው ነገሮች የኛ ሃላፊነት ያልሆኑ እኛን የማይመለከተንና ጊዜያችንን በከንቱ የሚጨርሱ ለኛ የማይመጥኑ ነገሮች ናቸው፡፡

በተለይ መፅሃፍ ቅዱስ የኑሮ ሃሳብና የባለጥግነት ምኞት የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ እንደሚያንቀው ይናገራል፡፡

የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡19

እነዚህ ነገሮች እግዚአብሄር ለእኛ ካለው የእገዚአብሄር ልጅነት የነገስታት ቤተሰብ አባልነት ደረጃ አንፃር ሲተያዩ ምንም ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች እግዚአብሄር በህይወታችን ካየልን ደረጃና ግብ ጋር ሲነፃፀሩ ተራና ጥቃቅኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ለእኛ ደረጃ የሚያስፈሩም ሆነ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም፡፡

ደረጃችን የእግዚአብሄር መንግስት ተወካይነት ነው፡፡ ደረጃችን የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ማስከበር እንጂ ስለሚበላና ስለሚጠጣ መጨነቅ ለክብራችን አይመጥንም፡፡

ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
ስለዚህ ነው አየሱስ እንዲህ ይላል፡፡

አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ሉቃስ 12፡32