Popular Posts

Monday, July 10, 2017

ህይወታችንን የምናባክንባቸው 8 መንገዶች

1.      ከእግዚአብሄር ውጭ ህይወትን መፈለግ
ሰው የተፈጠረው እና ዲዛይን የተደረገው በእግዚአብሄር እንዲኖር ነው፡፡ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡፡ ሰው የሚያየውና የሚከተለው የሚታየውን ቁሳቁስ ብቻ ከሆነ ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4
2.     እግዚአብሄር ያልመራንን ለመስራት መሞከር
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠው ነገር ሁሉ የተቀመጠው እግዚአብሄር በህይወታችን ላለው አላማ ነው፡፡ የምናባክነው ትርፍ ነገር የለም፡፡ ሰው በህይወቱ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ መፈለግና መከተል ትቶ እግዚአብሄር ያላለውን ነገር ሲያደርግ ህይወቱን ያባክናል፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
3.     ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር  
እግዚአብሄር ልዪ ለሆነ የህይወት አላማ እያንዳንዳችንን ጠርቶናል፡፡ የጎረቤታችንና የእኛ የህይወት አላማ ይለያያል፡፡ እኛ ግን ከጎረቤታችን ጋር ከተፎካከረን የማይገናኝና የማይሆን ነገር እያፎካከርን ነው፡፡ እኛ መወዳደር ያለብን እግዚአብሄር በህይወታችን ካስቀመጠው የህይወት ግብ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ግብ ከመታን ስኬታማ ነን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን አላማ ግብ ካልመታን ደግሞ ከማንም የበለጥን ቢመስለን ህይወታችንን እባክነናል፡፡  
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
4.     ባለፈው ህይወት ውስጥ መኖር
ሰው ያለፈውን ካልረሳ ደጋግሞ ይኖረዋል፡፡ ሰው ያለፈውን ካልረሳ ከወደፊቴ ይልቅ ያለፈው ይሻላል እያለ ነው፡፡ ሰው ያለፈውን ካልረሳ በወደፊቱ ተስፋ ቆርጧል ማለት ነው፡፡ ሰው ባለፈው ከኖረ በልቡ አርጅቷል ማለት ነው፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ፊልጵስዩስ 3፡13
5.     ስለኑሮ መጨነቅ
ሰው ድርሻውን የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ትቶ ስለኑሮ ከተጨነቀ ህይወቱን ያባክናል፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ የእግዚአብሄርን መንግስት መፈለግ እንዲሁም ስለኑሮ መጨነቅ አይችልም፡፡ ሰው ለሁለት ጌቶች መገዛት አይችልም፡፡ ለገንዘብ የሚገዛ ሰው ለእግዚአብሄር መገዛት አይችልም፡፡ ለኑሮ የሚጨነቅ ሰው ለእግዚአብሄር መንግስት የሚጠቅመውን ውድ ህይወቱን ያባክናል፡፡
ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ሉቃስ 12፡25
6.     በሚታይ መኖር
ሰው በሚታየው ብቻ የሚኖር ከሆነ የማይታየውን የእግዚአብሄርን መንግስት ማየት ካልቻለ ህይወቱን ያባክናል፡፡ ሰው በምድር ላይ ብቻ ስላለው ኑሮ ካሰብ ለዘላለም ስለሚኖርበት ህይወት ካላሰበና የዘላለም ህይወትን ካልያዘ ህይወቱን በከንቱ ያባክናል፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
7.       ነፍስን ማጉደል
ሰው ስለስጋው ብቻ ከሮጠ ነፍሱን ግን ከበደለ ብክነት ነው፡፡ ሰው ስጋውን ጎድቶ ነፍሱን ቢያለማ ይሻለው ነበር፡፡ ሰው ግን በምድር ላይ ሁሉንም አግኝቶ ዘላለማዊ ነፍሱን ግን ከጎዳ ምንም አይጠቅመቅውም፡፡
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ማቴዎስ 16፡26
8.       በፍቅር አለመኖር
ሰው ሁሉንም ነገር ትክክል አድርጎ ነገር ግን በፍቅር ካላደረገው ብክነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ሰው ምንም ነገር የሚያደርገው ከፍቅር መሆን አለበት፡፡ ሰው ግን ሁሉን ነገር አድርጎ በፍቅር ግን ካላደረገው ከንቱ ነው፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡2-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #ጭንቀት #ፉክክር #ምስጋና #ሁልጊዜ #ልብ #ለበጎስራሁሉ #ፀጋንሁሉ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Sunday, July 9, 2017

ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል

እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9
እግዚአብሄር ሙሉ ነው፡፡ እኛ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት የተቀበልን ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ሙሉ እንደሆነ ሁሉ በነገር ሁሉ ሙሉ ሊያደርገን ይችላል፡፡
ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ ዮሃንስ 1፡14
ሁልጊዜ
እግዚአብሄር ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እኛ እንኳን ንቁ ባልሆንበት ጊዜ እግዚአብሄር ግን ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሰው አይተኛም አያንቀላፋም፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ በስራ ላይ ነው፡፡  
ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17
በነገር ሁሉ
እግዚአብሄር ስለዝርዝር ጉዳያችን ግድ ይለዋል፡፡ እኛ አንኳን አንዳንድ ጊዜ ስለምንረሳው ጥቃቅን ጉዳያችን እግዚአብሄር ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ የተሳካለት ስለሆነ እኛ ልጆቹ በነገር ሁሉ እንዲሳካልን ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን ስላለው ስለእያንዳንዱ ሃላፊነት ሁሉ ጌታ ግድ ይለዋል፡፡ ይህ አይመለከተኝም የሚለው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ብቃትን ሊያበዛልን ይችላል፡፡
አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። ሉቃስ 12፡6-7
ብቃትን ሁሉ
ህይወት ብዙ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ህይወት አንድ መልስ የለውም፡፡ የተለያየ የህይወት አቅጣጫ የተለያየ መልስ ይፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ሃላፊነት ሃይልና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ የትኛው ጥያቄ በሃይል የትኛው ጥያቄ ደግሞ በጥበብ እንደሚመለስ ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርም በምድር ላይ አላማውን በሚገባ እንፈፅም ዘንድ ብቃትን ሁሉ ሊሰጠን ይችላል፡፡
ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ኤፌሶን 3፡10
ለበጎ ስራ ሁሉ
እግዚአብሄር እንድንሰራው ያዘጋጀውን መልካም ስራ ሁሉ መፈፀም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ወደምድር ያመጣን ስራውን ለመፈፀም የሚያስችልን ሃይል አዘጋጅቶ ነው ፡፡ በምድር ስንኖር እግዚአብሄር ካዘጋጀልን በጎ ስራ አንጎድልም፡፡ ለበጎ ስራ ሁሉ የሚያስፈልገው ብቃት በእኛ ውስጥ አለ፡፡ በጎ ስራ ከሆነ ልንፈፅመው እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ላዘጋጀው በምድር ላይ ሰርተን ለምናልፈው በጎ ስራ ሁሉ ብቃቱ አለን፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ፀጋን ሁሉ
ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ካለሃይል ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ በሃይል ደግሞ ማድረግ የማይቻል ምንም ነገር የለም፡፡ በፀጋ ሁሉም ይቻላል፡፡ በእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል ሁለም ይከናወናል፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ ሁሉ ይሳካል፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡10
እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #እውቀት #ምስጋና #ሁልጊዜ #ልብ #በነገርሁሉ #ብቃትንሁሉ #ለበጎስራሁሉ #ፀጋንሁሉ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, July 8, 2017

ፍቅር እና ራስ ወዳድነት

አለምን የሚመሩት የፍቅርና ራስ ወዳድነት ምክኒያቶች ናቸው፡፡ በህይወት የተሳካለት ለመሆን የፍቅርንና የራስ ወዳድነትን ልዩነት መረዳት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ፍቅርን በትክክል ስለማይረዱ ራስ ወዳድነትን ፍቅር ያደርጉታል፡፡ ራስ ወዳድነትና ፍቅር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለፍቅርና ስለራስ ወዳድነት ለመረዳት ፍቅርና ራስ ወዳድነት ስለባህሪያቸው መረዳት ወሳኝ ነው፡፡
ፍቅር ሙሉ ነው ራስ ወዳድነት ግን ጎዶሎ ነው
ፍቅር የተቀበለ ፣ የረካና የሞላለት ነው፡፡ መውደድ ፣ መስጠትና ማካፈል የሚችለው ሙሉ የሆነ ሰው ነው፡፡ ጎዶሎ የሆነ ሰው ከሌላው ይጠብቃል እንጂ መስጠትን አያውቅም፡፡ ሙሉ የሆነ ሰው ሊሰጥና ሊያካፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የለኝም ይጎድለኛል ከሚል የምስኪንነት አስተሳሰብ ይመነጫል፡፡ 
እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡33
ፍቅር ድፍረት አለው ራስ ወዳድነት ፈሪ ነው
ፍቅር ብሰጥም አይጎድለኝም ብሎ ያስባል፡፡ ፍቅር ብሰጥም ይሰጠኛል ብሎ ያምናል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ብለቀው አጣዋለሁ ብሎ በስጋት ይኖራል፡፡
ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38
ፍቅር ትሁት ነው ራስ ወዳድ ግን ትእቢተኛ ነው
ፍቅር ሌላው ከእርሱ እንደሚሻል ያስባል፡፡ ራስ ወዳድነት እርሱ ከሁሉ እንደሚሻል ያስባል፡፡ ፍቅር ሌሎችን ለማገልገል እንደተፈጠረ እድለኛ ሰው ሲመለከት ራስ ወዳድነት ግን ሌሎች እርሱን እንዲያገለግሉት የተፈጠሩ መጠቀሚያዎች አድርጎ በትእቢት ያስባል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3-4
ፍቅር አገልጋይ ነው ራስ ወዳድነት ተጠቃሚ ነው
ፍቅር ሌሎችን እንዲያገለግል እንደተፈጠረ ያውቃል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ሰው እርሱን እንዲያገለግለው ይፈልጋል፡፡ የፍቅር ሰው ሌሎችን የሚባርክ መልካም ነገር በእርሱ እንዳለ ያውቃል፡፡ ያንን መልካም ነገር ካለስስት ለሌሎች ይሰጣል፡፡ ራስ ወዳድነት  በእርሱ ያለውን ለሌሎች የሚጠቅመውን በጎነት አያየም፡፡ ራስ ወዳድነት የእርሱ በጎነት በሌሎች እንደተያዘ ይመስለዋል፡፡
ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ ማቴዎስ 20፡27
ፍቅር ደስተኛ ነው ራስ ወዳድ ሃዘንተኛ ነው
ፍቅር የሚቀናበት ሙሉ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የሚታዘንለት መከረኛ እና ሃዘንተኛ ነው፡፡ ፍቅር ደስ የሚሰኘው በማይለወጠው በእግዚአብሄር ስለሆነ ሁሌ ደስተኛ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ደስ የሚሰኘው በቁሳቁስ ስለሆነ ደስታው ተለዋዋጭ ነው፡፡
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
ፍቅር ለመኖር ብዙ አያስፈልገውም ራስ ወዳድነት ምንም ነገር አይበቃውም
ፍቅር ባለው ነገር ይረካል ባለው በነገር ሌሎችን ያገለግላል፡፡ ፍቅር ባለው ነገር እንዴት እንደሚኖር ያውቃል፡፡ ለራስ ወዳድነት ለእርሱ ምንም ነገር በቂ አይደለም፡፡ ፍቅር የተባረከበትን በረከት ያያል ፣ ያከብራል እውቅናም ይሰጣል፡፡ ራስ ወዳድነት የጎደለውና የሌለው ላይ ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ 
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6
ፍቅር በእርሱ ዘንድ ያለው ለሌሎች ሰዎች እንደሆነ ራስ ወዳድነት ደግሞ በሌሎች ውስጥ ያለው ለእርሱ እንደሆነ ያምናል
ፍቅር ለሌሎች የሚጠቅም ሌሎችን የሚያነሳ ሌሎችን የሚያሻግር ስጦታዎች በእርሱ እንዳለ ያምናል፡፡ ፍቅር በሌሎች ላይ ዋጋን ለመጨመር ፣ ሌሎችን ለማነፅ ፣ ሌሎችን ለመገንባት ፣ ሌሎችን ለማፅናናት እና ለማፅናት ተግቶ ይሰራል፡፡ ራስ ወዳድነት ሌሎች ካልረዱኝ ፣ ሌሎች ካልሰጡኝ ፣ ሌሎች ካላሰቡኝ ዋጋ የለኝም ብሎ ያስባል፡፡ ፍቅር ለሌሎች የሚጠቅም ነገር በእርሱ እንዳለ ሲያምን ራስ ወዳድነት ግን ምስኪንነት አስተሳሰብ ያለው ከመሆኑ የተነሳ እጅግ ሃብታም ካልሆነ ከታላቅ ከውርደቴ ሊያነሳኝ አይችልም ብሎ ያስባል፡፡
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10
ፍቅር በሌለው ያምናል ራስ ወዳድነት ራሱ ብቻ የምናል
ፍቅር ሌላው እንደሚነሳ ፣ እንደሚሄድ ፣ እንደሚሳካና እንደሚከናወን ያምናል፡፡ ፍቅር ሌላውን ስለሚያምን የሌላው መሳካት የእርሱ መሳካት እንደሆነ ይቆጥራል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከእርሱ ውጭ ማን እንዳማይሳካለት ፣ ማንም እንደማይከናወንለትና ማንም እንደማይወጣ ስለሚያስብ በሌላው ላይ መዝራት ብክነት ይመስለዋል፡፡
ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7
ፍቅር ኩሩ ነው ራስ ወዳድነት ስግብግብ ነው
ፍቅር አስቀድሞ የረካ ስለሆነ ቢጠቅሙትም እንኳን የማያደርጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍቅር የሚንቀው ጥቅም አለ፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ጥቅም ሆነ የሆነውን ሁሉ ነው የሚውጠው፡፡
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ፍቅር ክብሩን ያውቃል ራስ ወዳድነት መዋረዱን ያያል
ፍቅር እንደከበረ ያውቃል፡፡ ፍቅር ከዚህ በላይ ሊከብረው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የሚታየው መዋረዱ ነው፡፡ እንዴት ከውርደቱ እንደሚወጣ ሌት ተቀን ያቅዳል ያልማል፡፡
ፍቅር ሌት ተቀን የሚያስበውና የሚያተኩረው እርሱ በሚሰጠው በሚባርከው በሚጠቅመውንና በሚያካፍለው ላይ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ሌት ተቀን የሚያስበውና የሚያተኩረው ለእርሱ በሚያገኘው በሚጠቀመውና በሚተርፈው ነገር ላይ ነው፡፡ ፍቅር ሰውን የሚፈልገው ለሰውየው ጥቅም ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ሰውን እንኳን እወድሃለሁ የሚለው የሚጠቀመው ነገር እስካለ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ግን ሌላው ሲደክም ያን ጊዜ ነው ይበልጥ እንደሚያስፈልግ የሚረዳው፡፡
. . . ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡12
ፍቅር ማንነቱን ያውቃል ራስ ወዳድነት ማንነቱን አያውቅም
ፍቅር ማን እንደሆነ ስለሚረዳ ለመውደድ ለማካፈል ለማንሳት ለመበረክ አይከብደውም፡፡ ራስ ወዳድነት ስለራሱ እርግጠኛ ስላይደለ መውደድ ለሌች መፍሰስ አይችልም፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-4
ፍቅር ይተጋል ራስ ወዳድነት ይመኛል
ፍቅር እውነታን ይቀበላል፡፡ ካለበት ተነስቶ ይተጋል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን በእድል ብቻ ያምናል፡፡ ሁሌ ይመኛል ይፈልጋል፡፡
ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። ምሳሌ 21፡26  
ፍቅር ደፋር ነው ራስ ወዳድነት ግን ፈሪ ነው
ፍቅር ድፍረት አለው፡፡ ፍቅር ብሰጥም አይጎድልብኝም የሚል መተማመን አለው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከፍርሃት ይመነጫል፡፡ ራስ ወዳድነት ይጎድልብኛል አጣለሁ ከሚል የፍርሃት ስሜት ይመነጫል፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። ዕብራውያን 10፡34-35
ፍቅር ባለጠጋ ነው ራስ ወዳድነት ደሃ ነው
ፍቅር የሞላለት ነው፡፡ ፍቅር የረካ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የተራበ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የእጦት የጉድለት የድህነት ምልክት ነው፡፡
የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25
ፍቅር ሰጪ ነው ራስ ወዳድነት ንፉግ ነው
ፍቅር የሚታወቀው በመስጠት ነው፡፡ ፍቅር የሚታወቀው በማካፈል ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የሚታወቀው በመቀበል በማስወጣት በመበዝበዝ ነው፡፡ ፍቅር ሰጪ ሲሆን ራስ ወዳድነት ግን ጠባቂ ነው፡፡ ፍቅር ሲያካፍል ራስ ወዳድነት ግን የተራበ ጠባቂ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ሰዎችን ፍቅር በመስጠት በማስተላለፍ በመጠቀም ይረካል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን በመሰብሰብ በማከማቸት በማጋበስ ይረካል፡፡ ፍቅር ሌሎችን በማንሳት በሌሎች ላይ ዋጋን በመጨመር ይረካል፡፡ ራስ ወዳድነት ራሱ ላይ ብቻ በማከማቸት ይረካል፡፡  ፍቅር ራሱን በሌሎች ያበዛል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከራሱ ጋር ይሞታል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ምስኪንእኔ #ድፍረት #መስጠት #ማካፈል #ሙላት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #መታበይ #ራስወዳድነት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, July 7, 2017

ስለፈተና የቃሉ የጥበብ አንኳሮች

ፈተና ፈተናነው፡፡ ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ ፈተና ሲገቡበት የሚወጡበት አይመስልም፡፡ ፈተና ሳይመጣ ደግሞ የሚመጣ አይመስል፡፡ ፈተና አስጨናቂ ነገር ነው፡፡ ስለፈተና የእግዚአብሄር ቃል የሙሉውን ከተረዳን በፈተና እንዴት መቋቋም እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ስለፈተና ከተረዳን ፈተና ማስፈራቱን ባያቆምም ይቀንሰዋል፡፡ ምክኒያቱም ፈተና ይመጣል፡፡ ፈተና ቢመጣ አይደለም የሚባለው ፈተና ሲመጣ ነው የሚባለው ምክኒያቱም ዝናብ ጎርፍ ነፋስ ይመጣል፡፡  
ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ማቴዎስ 7፡25
1.      ለፈተና እንግዳ አትሁን
በአንድም በሌላ መልኩ ያለኸው በፈተና ውስጥ ነው፡፡ እንዲሁም በአንድም በሌላም መልኩ ሌላ ፈተና እየመጣ ነው፡፡ ፈተና ሊነካህ የማይች ሰው አድርገህ ራስህን አትቁጠር፡፡ ፈተና ቢመጣም ገፈተናውን ልታልፍ እንደምትችል በትህትና አስብ፡፡
በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። ዮሃንስ 16፡33
2.     የፈተናን አላማና ውጤት ተረዳ
የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል በህይወታችን የምንወርሰው በትግስት ነው፡፡ ፈተና ትእግስትን በህይወታችን ይሰራል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ ሮሜ 8፡3-4
3.     በፈተናው ላይ አታተኩር
አንተ የእግዚአብሄር ልጅ ነህ፡፡ አንተ በምድር ላይ የእግዚአብሄርን አላማ እንድታስፈፅም የተላክ የእግዚአብሄር መልክተኛ ነህ፡፡ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስብህ በፈተና ግብ ላይ እንጂ በፈተናው ላይ ብቻ አታተኩር፡፡  
እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራዊያን 12፡1-2
4.     እግዚአብሄር በክፉ እንደማይፈትን ተረዳ
ፈተና ሲመጣ እግዚአብሄር ሊጥልህ እንዳማይፈትንህ ተረዳ፡፡ ለክፉ የመጣውን ፈተና እግዚአብሄ ለመካለም ለውጦ አንተን ያጠራሃል፡፡ እግዚአብሄር ግን ሊጥል እንደማይፈትንህ አትርሳ፡፡ እግዚአብሄር በክፉ እንደማይፈትንህ ስትረዳ ከፈተናው በአሸናፊነት እንደምትወጣ ጉልበት ታገኛለህ፡፡
ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ያዕቆብ 1፡13
5.     ከፈተና ግብ ለማምለጥ አትሞክር
ከፈተና ለማምለጥ ካልሞከርክና ከታገስከው ትግስት ሙሉ ሰው ያደርግሃል፡፡ ትግስት ከአንተ ላይ የማያስፈልገውን ነገር ያራግፋል፡፡ ትግስት የሚያገኘው እግዚአብሄር የማይወደውን ስጋዊ ባህሪ እንጂ አንተን አይደለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን የሚያሳዝነውን ስጋዊ ምኞት እንዲገድል ተባበር፡፡ ከፈተና ይዘህ የምትወጣውን በሌላ በምንም መንገድ የማይገኘውን ሙላት  አስብ፡፡ በፈተናው ላይ ሳይሆን ከፈተና ውስጥ በምታገኘው ነገር ላይ አተኩር፡፡ ፈተናው በህይወትህ በሚሰራው ወሳኝ ስራ ላይ ካተኮርክ በፈተናው ለመፅናት ጉልበትን ታገኛለህ፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ያዕቆብ 1፡2-4
6.     በፈተና ወቅት በጥንቃቄ ኑር
በፈተናው ውስጥ ስታልፍ ሰይጣን በፈተናው ውስጥ ያዘጋጀውን ወጥመድ ውስጥ አለመውደቅህን እርግጠኛ ሁን፡፡ በፈተናው ውስጥ በእግዚአብሄር ህግ መኖርህን እርግጠኛ ሁን፡፡ በፈተናው ውስጥ ቸኩለህ የተሳሳተ ውሳኔ ላለመወሰን ታገስ፡፡ የሰይጣን አላማ ሊያረክስህ ነውና በፈተናው ጊዜ በንፅህና መመላለስህን እርግጠኛ ሁን፡፡ በፈተናው ጊዜ በህጉ መጫወትህን እርግጠኛ ሁን፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ኤፌሶን 5፡15
7.     በፈተናው ውስጥ በጌታ ደስ ይበልህ
የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ያዕቆብ 1፡2-3
8.     ከፈተናው የተሻለ ነገር ማውጣትህን እርግጠኛ ሁን
አንተን ለመጣል የመጣውን ፈተናውን መልሰህ ለራስህ ጥቅም አውለው፡፡ በፈተናው አትሸነፍ በመልካም ነገር አሸንፍ እንጂ፡፡ ክፉውን ቀኖች ዋጅተህ ለራስህ ጥቅም አውላቸው፡፡
ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ቆላስይስ 4፡5
9.     ጥበብን ጠይቅ
ማንኛውም ችግር መፍትሄ አለው፡፡ ማንኛውም ጥያቄ መልስ አለው፡፡ ለጊዜው ቢመስልም መልስ የሌለው ጥያቄ መፍትሄ የሌለው ችግር የለም፡፡ የፈተና ከባድነት መውጫውን አለማየት ነው፡፡ መውጫውን ማየት እንድትችል ጥበብን ከእግዚአብሄር ለምን፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡2-5
10.    ከፈተናው ውስጥ ምስጋናን ይዘህ ውጣ
በፈተናው ወቅት አመስግን፡፡ ምሰጋና ሲመቸን የምናቀርበው ብቻ ሳይሆን ሳይመቸን የምንሰዋው ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄርን እጅግ የሚጣፍጠው ምስጋና በአስቸጋሪ ነገር ውስጥ ሆነህ የምትሰዋው ምስጋና ነው፡፡ ከፈተናው ውሰጥ ምስጋናን ብቻ ይዘህ ውጣ፡፡ ከፈተናው ውስጥ እከሌ እንዲህ አደረገኝ አከሊትይ እንዲህ አደረገችኝ አትበል፡፡ ከፈተናው ውስጥ ይዘህ መውጣት ያለብህ ብቸኛ ትምህርት እግዚአብሄር መልካም ነው የሚል መሆን አለበት፡፡ ብዙ ቅዱሳን በተለያየ ከፍታና ዝቅታ አልፈዋል፡፡ ሁሉም ግን ሲወጡ እግዚአብሄር መልካመ ነው የሚል መረዳት ይዘው ነው የወጡት፡፡  
እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ናሆም 1፡7
ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ። መዝመር 50፡23
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #አምላክ #ፈተና #መከራ #ትግስት #ምሉአን #ፍፁማን #ደስታ #ምስጋና #ፅናት #ጥበብ #እምነት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ