Popular Posts

Sunday, November 22, 2020

ከእውነት_ጋር_እቆማለሁ!

 

ሰሞኑን የኢትዮጲያ መንግስት ሰራዊት ጁንታ ከሚለው ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ሰራዊት ጋር ወደ ጦርነት ውስጥ ገብቷል፡፡ ሁለቱም እነርሱ ትክክል እንደሆኑና ሌላው ወገን ስህተት እንደሆነ ሲናገሩ እንሰማለን፡፡

እኔም በዚህ ረገድ የራሴ አስተያየት ቢኖረኝም የራሴ አስተያየት ሙሉ ለሙሉ ትክክል ላይሆን ስለሚችል ላለመፃፍ ወስኛለሁ፡፡ አብዛኛው ሰው አንዱን በስሜት በሚደግፍበት ጊዜ የራሴ አስተያየት መፃፍ ለሚወዱኝና ለሚያከብሩኝ አንባቢዎቼ እንቅፋት ስለሚሆን እንዲሁም ደግሞ የእኔ የግል አስተያየቴ ምንም ስለማይጠቅም ትቼዋለሁ፡፡

ነገር ግን ከእግዚአብሄር ቃል እንፃር ግን የተረዳሁትን ለመፃፍ ልቤ ወደደ፡፡

እንደ ዜጋ የመንግስት መሪዎችን መታዘዝ ትክክል ነው፡፡ ግልፅ የሆነ የእግዚአብሄር ቃልንና ህሊናን የጣሰ ግልፅ ስህተት የሆነ ነገር አይዘዙት እንጂ ሰው የመንግስት መሪዎቹን በመታዘዙ አይሳሳትም፡፡

ሰው ከግል ጥላቻ ተጠብቆ መንግስትን ሰምቶ ወታደርነት ቢሄድና አገርንና ህዝብን ቢጠብቅ ምንም ስህተት የለበትም፡፡  ወንድምም ቢሆን እንኳን ሊገድለን የመጣን ሰው እንደ ግለሰብም እንደ ሃገርም መከላከል ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

ሰው ግን በጥላቻ እና በንቀት ተነሳስቶ ስለሚያደርገው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ነው አንድ ቀን በእግዚአብሄር ፊት መልስም ይሰጥበታል፡፡   

መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ
ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ የማቴዎስ ወንጌል 12፡35-36

ሁሉም ወገን እግዚአብሄር ከእርሱ ጎን ያለ ይመስለዋል ወይም ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር የሚቆመው እውነትን ከያዘው ሰው ጋር ነው፡፡

እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው። እርሱም፦ አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 5፡13-14

አሳየዋለሁ ብሎ በትእቢት ከሚነሳ መንግስትም ሆነ ግለሰብም ጋር እግዚአብሄር አይቆምም፡፡ እግዚአብሄር በጥላቻ ተነስቶ ሰውን ለማጥፋት ከሚንቀሳቀስ ግለሰብም ይሁን ቡድንም ጋር አይወግንም፡፡

እግዚአብሄር ከእውነት ጋር ይቆማል፡፡ ሰው ከእውነት በተቃራኒ ራሱን እንዳያገኝና እንዳይጨፈለቅ የሚያዋጣው ከእውነት ጋር መወገን ብቻ ነው፡፡ ተቃራኒዎቼ እውነት ይኖራቸው ይሆን? ብሎ መፍራት ጉዳዩን ከሌላው ወገን ለማየት እና በጭፍን ከመፍረድ ያድናል፡፡

አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። የሐዋርያት ሥራ 5፡38-39

ማንኛውም ገንዘብ ያለው ሰው ፣ ሃያል የሆነ ሰው እንዲሁም ጠቢብ የሆነ ሰው ቢሆን በእውነት ላይ ግን ተነስቶ ሊበረክት አይችልም፡፡ የትኛውም ሰው ከእውነት ጋር ሊወግን እንጂ እውነትን ሊለውጥ አይችልም፡፡    

ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡8

በአለም ታሪክ እግዚአብሄር በግለሰብ ህይወት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሃገር ጉዳይ ላይ ጣልቃ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ህዝቡን ስለሚወድ አለምን በፍቅር በሃይልና በጥበብ ያስተዳደራል፡፡ እግዚአብሄር በማይፈራው በትእቢተኛ ግለሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በትእቢተኛ ሀገር እና መንግስት ላይ ይነሳል፡፡ እግዚአብሄር በማን አለብኝነት ክፋት በሚሰራ ግለሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን  በትእቢተኛን መንግስት ላይ ይፈርዳል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ከተማንና አገርን ያዋርዳል፡፡

አቤቱ፥ ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍርድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና። መዝሙረ ዳዊት 82፡8

እግዚአብሄርን ፈርቶ ክፋት ላለማድረግ በመጠንቀቁ እንጂ ንጉስ በሰራዊቱ ብዛት አይድንም፡፡ ሰው በሃይሉ ብዛት ቢታመን እግዚአብሄርን ያሳዝናል እንጂ አያስደስትም፡፡

ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፥ ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ መዝሙረ ዳዊት 33፡16-18

አሸናፊው ማነ ነው ብትሉኝ ትሁት የሆነ እውነት ከእርሱ ጋር ያለችው እግዚአብሄርን የሚፈራ ቡድን አሸናፊ ነው፡፡ ተሸናፊው ማነው ብትሉኝ ትእቡተኛው በሃይሉ የሚተማመነው ይሸነፋል፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24

ከጥላቻና ከንቀት ተጠቃሚው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ ፀሎታችን መሆን ያለበት እግዚአብሄር በየደረጃው ላሉት መሪዎቻችን ጥበብን እንዲሰጣቸው ራሳቸውን ትሁት እንዲያደርጉና እግዚአብሄር እንዲፈሩ ነው፡፡  

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa .37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #እውነት #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ትህትና #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment