Popular Posts

Sunday, May 31, 2020

የነፍስ ብቻ ሳይሆን የስጋ ፈውስ ያስፈልገናል




ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፦ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ ወደ ዕብራውያን 10፡5
በመድር ላይ ለመኖር ለመንቀሳቀስ ለመውጣትና ለመግባት ስጋ ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስ እኛን ከሃጢያት የማዳን ስራ ለመስራት ስጋ አስፈልጎት ነበር፡፡
ኢየሱስ ምንም ሙሉ መንፈሳዊነት ቢኖረው በስጋ ውስጥ ባይኖር ኖሮ ግን የማዳንን አላማ ማስፈፀም አይችልም ነበር፡፡
የነፍስ መዳን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በምድር ላይ የምንፈፅመው የተለየ አላማ ባይኖረን ኖሮ ነፍሳችን እንደዳነ ወዲያው ወደጌታ እንወሰድ ነበር፡፡
እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንፈፅም የሰጠንን ራእይና አላማ ለመፈፀም ደግሞ በምድር ላይ መኖር አለብን፡፡ በጠንካራ እና በጤነኛ አካል በምድር ላይ ካልኖርን እና ሰይጣን በፈለገው ጊዜ የፈለገውን በሽታ የሚያደርግብን ከሆነ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈጸም ያቅተናል፡፡
እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና። አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡11-13፣16
እግዚአብሄር በክርስቶስ በኩል የነፍሳችንን መዳኛ መንገድ ብቻ ፈጽሞ ቢሄድ ሰይጣን በስጋችን ላይ የፈለገውን ቢያደርግ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ መፈፀም እንችልም ነበር፡፡
እግዚአብሄር ግን ለነፍሳችን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችን ስለሚኖርበት ስለስጋችን ሙሉ ዋጋን ከፍሏል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በመገረፉ ቁስል እንደተፈወስን የሚናገረው በምድር ላይ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም የነፍሳችን መዳን ብቻ ሳይሆን የስጋችን ብርታት አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡    
ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡24
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ስለሰዎች ነፍስ መዳን መስበክ ብቻ ሳይሆን ስለስጋቸውም ፈውስ በትጋት እና በቅናት ይፀልይ የነበረው ስለዚህ ነው፡፡
እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሐዋርያት ሥራ 10፡38
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment