Popular Posts

Wednesday, August 21, 2019

ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?



እግዚአብሄር ምንም ያህል መንገዱን እንድንከተል ቢፈልግም ነገር ግን የእግዚአብሄርን አላማ መሳት አለ፡፡ እግዚአብሄር ምንም ያህል እንዳንስት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ቢያዘጋጅም ነገር ግን መሳት በህይወታችን ይከሰታል፡፡ መሳት የማይያዝ የማይጨበጥ ሃይማኖታዊ ሃሳብ ሳይሆን እውን በእለት ተእለት ህይወታችን ሊከሰት የሚችል ክስተት ነው፡፡
በህይወታቸው የእግዚአብሄርን መንገድ የሚጠብቁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በህይወታቸው የእግዚአብሄርን መንገድን የሚስቱ ሰዎች አሉ፡፡ በህይወታቸው መሄድ የማይፈልጉበት ቦታ ራሳቸውን የሚያገኙ ሰዎች አሉ፡፡
እኛ የእግዚአብሄርን መንገድ መሳት ከማንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እንዳንስት ቢፈልግም ነገር ግን መሳት በሰው ልጆች ህይወት ላይ የሚከሰት ያለ ነገር ነው፡፡ መንገዱን እንዳንስት እግዚአብሄር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ቢያዘጋጅም እንኳን መሳት እውን ነው፡፡ መንገዱን እንዳንስት እግዚአብሄር ካዘጋጃቸው እጅግ ብዙ ነገሮች አንፃር መሳት ከባድ ቢሆንም ነገር ግን እግዚአብሄርን መንገድ ልንስት አንችለም ማለት ግን በፍፁም አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር ፍቅር አንፃር ለሰው ከመሳት ይልቅ አለመሳት ቢቀለውም ነገር ግን መሳት የለም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን እየፈለግን መሳት ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ካልተጠነቀቅን ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 7፡17
ልስት አልችልም ብለን ስላሰብን ብቻ አንስትም ማለት አይደለም፡፡ ከሚስቱ ሰዎች አብዛኛዎቹ ከመሳሳታቸው በፊት መሳት የሚባለው ነገር እኔ ላይ ላይ አይደርስም ብለው አስበዋል፡፡ የማይጠነቀቀውና የሚስተው ልስት አልችልም ብሎ የሚይስብ ሰው ብቻ ነው፡፡  
ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ” ያድንሃል። መጽሐፈ ምሳሌ 2:11
እኛም ብዙ ጊዜ ለዚህ አሳልፈ አልሰጥም ብለን ላሰብንለት ነገር ተሰጥተን ራሳችንን አግኝተነዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ በእኔ ላይ አይሆንም ብለን ያሰብነው ነገር ሆኖብን አይተናል፡፡
ምንም ያህል ነገሮች የምናይና የምናውቅ ብንሆን የማናያቸው ነገሮች አሉ ብለን ማሰብ እና የእግዚአብሄርን እርዳታ በቀጣይነት መፈለግ ጥበብ ነው፡፡  
የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል። መጽሐፈ ምሳሌ 21፡2
ጌታ  ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል ባለ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ እኔ እሆንን? ይሉ ጀመር፡፡
ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። የማቴዎስ ወንጌል 26፡21-22
ማነው እርሱ አሳልፎ የሚሰጥህ ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እኔ እሆንን ማለት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እርሱ ማነው የሚለው ብቻ ሳይሆን እኔ እሆንን ማለት ትህትና ነው፡፡ አንተ አይደለህም ብሎ ሊመሰክር የሚችል የእግዚአብሄር ቃልና የእግዚአብሄር መንፈስ ብቻ እንጂ እኛ ራሳችን አይደለንም፡፡  ወደድንም ጠላንም አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ውስጥ ያለው ስጋ እኛም ውስጥ ይኖራል፡፡ ይሁዳን ያሳሳተው ሰይጣን እኔን ሊያሳስተኝ አይችልም ብሎ አለመጠንቀቅ በእርግጥ መሳትን ያስከትላል፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋርያው ፍራ እንጂ የትቢትን ነገር አታስብ ያለው ለዚህ ነው፡፡ የሚወድቁት ልወድቅ አልችልም ብለው የማይጠነቀቁ ሰዎች ናቸው፡፡ የሚወድቅ ሰው ምልክቱ ልወድቅ አልችልም ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ አንተ ልትወድቅ እስከማትችል ድረስ መጠንቀቅ የለብህም ብሎ ካሳመናችሁ ሰይጣን እንጂ እግዚአብሄር ሊሆን ፈፅሞ አይችልም፡፡  
መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። ወደ ሮሜ ሰዎች 11፡20
ታላቁ ሃዋርያው ጳውሎስ እንዳይስትና እስከመጨረሻው ፀንቶ ለመቆም የሚያደርገውን ጥንቃቄ እያየን እኔ አልስትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #መንገድ #ድምፅ #ጌታ #መሳት #ስህተት #ትእቢት #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጥንቃቄ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment