Popular Posts

Saturday, August 17, 2019

በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ


እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16 

ክርስትና የሚቻለው በእግዚአብሄር እርዳታ ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር እርዳታ ውጭ እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻለም፡፡ እግዚአብሄር በሚያስችል ፀጋው ካላስቻለን ፈቃዱን አድርገን እግዚአብሄርን የሚያስደስት ህይወት ሊኖረን አይችልም፡፡ 

ለእግዚአብሄር መኖር እየፈለግን አንዳንድ ጊዜ አቅም እናጣለን ይደክመናል፡፡ ለእግዚአብሄር እንዴት መኖር እንዳለብን እናውቃለን ነገር ግን ጉልበት እንደከዳን ይሰማናል፡፡ በየት መንገድ መሄድ እንዳለብን እናውቃለን ነገር ግን ተጨማሪ እርምጃ ለመራመድ ጉልበት እንዳነሰን ይሰማናል፡፡ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንፈልጋለን ነገር ግን ከተለያየ ምክኒያት የተነሳ ይታክተናል እርዳታን እንፈልጋለን፡፡ 

ለጌታ ለመኖር ፈቃዱን ለማድረግና በነገር ሁሉ እርሱን ለማስደሰት ያለን ብቸኛ አማራጭ ወደ እርሱ መሮጥ ነው፡፡ በኑሮዋችን እርሱን ማስደሰት የምንችልበትን በሚያስፈልገን በትክለኛው ጉልበት የምናገኘው ከፀጋው ዙፋን ነው፡፡ 

የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ ሁልጊዜ ሊረዳ ሊደግፍ ፈቃደኛና የተዘጋጀ መልካም አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ እርዳታውን የሚፈልጉትን በመርዳት የተካነ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት በህይወታችን የሚገጥመንን ማንኛውንም ተግዳሮት ለማለፍ የሚያስችል ብቃትን የምናገኘው ከእርሱ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ ከልባቸው እርዳታውን የሚፈልጉትን ለመርዳት አይኖቹ በምድር ላይ ስለሚመላለሱ ነው፡፡ 

እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 16፡9 

የእግዚአብሄርን ፈቃድ ላለማድረግ ምንም ሰበብ የለንም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችለንን ፀጋ እንድንቀበል ወደፀጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ፡፡ ይበልጥ ወደ ፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን ይገለጣል፡፡ ይበልጥ ወደፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ በድካማችን ላይ የእግዚአብሄር ፀጋ ብርታት ይገለጥበታል፡፡ ይበልጥ ወደፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ የእግዚአብሄር ፀጋ ድካማችንን ይሸፍናል፡፡ ይበልጥ ወደ ፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ ድካማችን በብርታት ይለወጣል ለእግዚአብሄርም ለመኖር አቅም እናገኛለን፡፡ 

ወደ ፀጋው ዙፋን መቅረብ ያለብን ደግሞ በእምነት ነው፡፡ ስለአንድ የህይወታችን ጥያቄ ወደፀጋው ዙፋን ከቀረብን በኃላ እግዚአብሄር የሚያስችለውን ፀጋ እንደሰጠን አምነን መሰማራት አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ እንደተቀበልን የምናውቀው በእምነት እንጂ ወደ ፀጋው ዙፋን እንደቀረብን እየበረረ መጥቶ የሚገባብን በተፈጥሮአዊ አይን የሚታየ ፀጋ የለም፡፡ እግዚአብሄር ሊደግፈን እንደሚፈልግ በማመን ወደፀጋው ዙፋን ከቀረብን በኃላ ታምነን መሰማራት አለብን፡፡ 

በእግዚአብሔር ታመን፥ . . . ታምነህም ተሰማራ። የዳዊት መዝሙር። 37፡3 

እንደፈቃዱ እንደፀለይን ካመንን እንደተቀበልን እናውቃለን፡፡ 

በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፡14-15 

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ 

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes 

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos 

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #የሚረዳንን #ፀሎት #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ.

No comments:

Post a Comment