Popular Posts

Tuesday, April 26, 2016

የትንሳኤው ሃይል ለእኛ ነው

ሰዎች ለምዕተ አመታት ሞት የበለጠ ኃይልን ሲፈልጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፡፡  ሞት እጅግ ታላቅ ሃይል ስላለው የቱም ሰብዓዊ ፍጡር ለሞት መድሃኒት ሊያገኝለት አልቻለም፡፡

የምስራች!

ኢየሱስ ከሙታን ሲነሳ ሃያሉ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ተነሳ፡፡ በምድር ላይ በወቅቱ በጣም ኃያል የነበረውን ሞትን ስላሸነፈ የትንሣኤ ኃይል ከታላላቅ ሃይላት ሁሉ በላይ ልዕለ ሃያል ሊሆን በቅቶዋል፡፡  

እየሱስ ከሙታን በመነሳቱና ሞት በህይወት ስለተረታ አሁን በትንሳኤው ሃይል በማመን  ከእግዚአብሄር ጋር በህያውነት ለዘላለም  መኖር እንችላለን፡፡

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10

እየሱስ የሞተው ስለራሱ ሃጢያት አይደለም፡፡ እየሱስም ከሞት የተነሳው እኛን ከሞት ሃይል በላይ ለማድረግ ነው፡፡ እየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሳ ስናምን ይህ የትንሳኤ ሃይል በህይወታችን መስራት ይጀምራል፡፡ ኢየሱስ ከሞት ተነሳው እኛ ይህንን የትንሳኤ ሃይል እንድንለማመድ ነው፡፡

እየሱስን ባመንን በሁላችን ውስጥ ከሙታን በሃይል የተነሳው እየሱስ ይኖራል፡፡ እየሱስን ከሙታን ያስነሳው ያው ተመሳሳይ ሃይል በእኛ ውስጥ ይሰራል፡፡ እየሱስ በመንፈስ በልባችን የሞኖረው ከዚህ የትንሳኤ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ነው፡፡ እየሱስ በልባችን ስለሚኖር ከአሸናፊዎች በላይ ነን፡፡

በኢየሱስ ትንሳኤ "ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ" የሆነ ሃይል ታይቶዋል፡፡ ኤፌሶን 1፡20-2

ኢየሱስ በትንሳኤ የጠላትን ሃይል ሁሉ አሸንፎታል፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ ስለ እየሱስ የጠላትን ሃይል ሁሉ ፈፅሞ ስለማሸነፍ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2:15

እኛም በትንሳኤ ከእየሱስ ጋር ተነስተናል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር በአብ ቀኝ ተቀምጠናል፡፡

ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6

እየሱስን ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሄር አሰራር ያመንን ሁላችን ከእየሱስ ጋር ተነስተናል፡፡ እየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ እኛንም በሰማያዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር በአብ ቀኝ አስቀምጦናል፡፡ በዚህም በሞት ላይ ስልጣን ባለው በዲያቢሎስ ሃይል ሁሉ ላይ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10:19

ቤተ-ክርስቲያን እኛ የእግዚአብሄር ህዝቦች በምድር ላይ አካሉና የእየሱስ ክርስቶስ ሙላት ስለሆንን በእየሱስ የሚሰራው የትንሳኤ ታላቅ ሃይል ሁሉ ለእኛ ነው፡፡

ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። ኤፌሶን 1፡18-22

No comments:

Post a Comment