Popular Posts

Wednesday, April 27, 2016

እኛም ተነስተናል

ትንሳኤ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ ብዙ ሰዎች የትንሳኤን ትርጉምና ከእኛ ህይወት ጋር ያለውን ተዛምዶ በፍፁም አይረዱትም፡፡ በዚያም ምክኒያት የትንሳኤን ሙሉ ጥቅም በህይወታቸው ተጠቃሚ መሆን አይችሉም፡፡

ለአንዳንዶች የአመት አንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ እየሱስ ስለሃጢያታችን ይቅርታ ከሙታን የተነሳበት ቀን ነው፡፡

የትንሳኤው አላማ ይህንን የሚያጠቃልልም ቢሆንም ከዚህ ሁሉ ግን ያለፈ ትርጉም አለው፡፡ እየሱስ በመስቀል የሞተውና በሶስተኛ ቀን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው የሃጢያታችንን ዋጋ ለመክፈል ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ ከሃጢያት በላይ ሆነን እንድንኖር ይህን የሃጢያት ስጋችንን በመስቀል ላይ ለመስቀልና ለመግደል ነው፡፡

እየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞትና ሲነሳ እኛም ለሃጢያት ሞተን ለእግዚአበሄር ፅድቅ ህያዋን እንድንሆን ራሳችነነ በእምነት እንድናስተባብር ነው፡፡

እየሱስ በመስቀል ላይ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ያደረገው ለራሱ አልነበረም፡፡ እየሱስ በመስቀል ላይ የሞተውና የተነሳው ለእኛ ነው፡፡ እየሱስ ይህንን ሁሉ ያደረገው እኛን ተክቶ ነው፡፡ እየሱስ ሲሞትና ሲነሳ የእኛን ታሪክ እየሰራው መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
እየሱስ ሲሞት የሞትኩት እኔ ነኝ ብለን መውሰድ እየሱስ ሲነሳ እኔም ከእርሱ ጋር ተነስቻለሁ ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡
እየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የእኛ የሃጢያት ስጋ ከእየሱስ ስጋ ጋር አብሮ ተሰቅሎዋል ፡፡ እየሱስ ሲሞት የሃጢያት ስጋችን አብሮ ሞቷል፡፡
የስቅለቱ ታሪክ የእየሱስ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የእኛም ታሪክ ነው፡፡ በዚህ በእግዚአብሄር አሰራር እየሱስ ሲሞትና ከሞት ሲነሳ በእኛም ህይወት ውስጥ የተከናወነ ነገር አለ፡፡ ይህም፡-
  • 1.ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል፡፡


ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20

  • 2.     ለሃጢያት ሞተናል

ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ሮሜ 6፡2

  • 3.     ከሃጢያት እስራት ነፃ ወጥተናል

ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። . . . አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። ሮሜ 6፡18 እና 22

  • 4.     ሃጢያት በእኛ ላይ ስልጣን የለውም

ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14

  • 5.     በአዲስ ህይወት ለመመላለስ ከሞት ተነስተናል፡፡

እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሮሜ 6፡4

  • 6.     የፅድቅ ባሪያዎች የእግዚአብሄር አገልጋዮች ተደርገናል

አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። ሮሜ 6፡22

  • 7.     ለሃጢያት ሙት ለእግዚአብሄር ህያዋን ነን

እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። ሮሜ 6፡11

No comments:

Post a Comment