በነገር ሁሉ በእግዚአብሄር ላይ እንዳንደገፍ የማያቋርጥ ፈተና
አለብን፡፡ እምነት ለስጋ አይመቸውም፡፡ ስጋ የሚፈልገው በስጋ አይን የሚታይ መተማመኛን እንጂ በእግዚአብሄር መታመንን አይደለም፡፡
ስጋ በፍፁም በእግዚአብሄር መታመን ስለማይፈልግ ሌሎችን አማራጮች
ሁሉ ይጠቀማል፡፡
እየሱስ ስለዘሪው ምሳሌ ሲያስረዳ የእግዚአብሄር ቃል በሙላት
ሊሰራባቸው ስላልቻለውና ሙሉ ፍሬ ማፍራት ስለማይችሉ ሰዎች ችግር
ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም
ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8፡14
በዚህ ቃል Çበሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾትÈ የሚለውን በማርቆስ ላይ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡፡
Çየዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር
ምኞትÈ ማርቆስ 4፡19
ስጋ ነው ቶሎ ቶሎ ሃብትን አከማችቶ በእግዚአብሄር ላይ ከመታመን
ነፃ መውጣት የሚፈልገው፡፡
ሰው በአለም ላይ ያለው ገንዘብ ሁሉ ቢኖረው ህይወት ይኖረዋል
ማለት አይደለም፡፡ በህይወት ገንዘብ የማይሰራቸው እጅግ በጣም ብዙ
ነገሮች አሉ፡፡ እንዲያውም በህይወት በጣም ወሳኝ ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸው ነገሮች አይደሉም፡፡
ሰው ሙሉ በሙሉ በሁሉም የህይወቱ አቅጣጫ በእግዚአብሄር ላይ
እንዲደገፍ ዲዛይን ስለተደረገና ስለተሰራ በሁሉም የህይወቱ አቅጣጫ ሁል ጊዜ እግዚአብሄር ያስፈልገዋል፡፡
የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ምሳሌም
ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም፦ ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤
ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤
ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ
ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር
ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ
12፡15-21
ይህ ባለጠጋ እግዚአብሄርን ከመታመን ለመገላገል ንብረትና ሃብት
አከማችቶዋል፡፡ የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛት ስለመሰለው በእግዚአብሄር ላይ ከመታመን ጡረታ ለመውጣት ቸኩሎዋል፡፡
የሰው ህይወቱ ግን በገንዘቡ ብዛት አይደለም፡፡ ትንሽ ገንዘብ
ያለው ትንሽ ህይወት የለውም፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለው ብዙ ህይወት የለውም፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለው ትንሽ ህይወት ሊኖረው ይችላል፡፡
ሰው ደግሞ ትንሽ ገንዘብም ኖሮት ብዙ ህይወት ሊኖረው ይችላል፡፡ የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛትና ማነስ አይወሰንም፡፡
ይልቁንም የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛት ሳይሆን በእምነቱ ብዛት
ነው፡፡
ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2:4
ሰው ግን የተፈጠረውና ዲዛይን የተደረገው በሁሉ ነገሩ በእግዚአብሄር
ላይ ብቻ እንዲታመን ነው፡፡
ስለዚህ ነው የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ ማቴዎስ 6:11 በማለት እንድንፀልይና በየእለቱ በእግዚአብሄር ላይ እንድንደገፍ የሚያስተምረን፡፡
መቼም ቢሆን በእግዚአብሄር ላይ ያለንን እምነት በሚታይ ነገር
መለወጥ የለብንም፡፡ እንዲያውም ከጊዜ ወደጊዜ በእግዚአብሄር ላይ ያለንን መታመናችንን ማብዛት ነው የሚገባን፡፡
ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። ሮሜ 1፡17
No comments:
Post a Comment