Popular Posts

Follow by Email

Sunday, April 24, 2016

የሰላም እንቅፋት

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ዮሃንስ 14፡27
ነገር ግን እኛ ነን ሰላማችንን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለብን ፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ እኛ ይህንን የተሰጠንን ሰላም እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያስተምረን፡፡

ሰላማችንን ሊሰርቁ የሚመጡ የሰላማችን ጠላቶች አሉ እነርሱም፡-

·        እግዚአብሄር እየመራን እንደሆነ አለማወቅ፡፡

እግዚአብሄርን በሁለንተናችን መከተል የልባችን መሻት ስለሆነ የእግዚአብሄርን ምሪት የሳትን ሲመስለን ሰላማችን ይሰረቃል፡፡ እግዚአብሄር ግን አሁንም እየመራን ነው፡፡ የእግዚአብሄር መሪነት አስተማማኝነቱ ከተመሪዎቹ ከእኛ ችሎታ ሳይሆን ከመሪው ከእግዚአብሄር የመምራት ችሎታ ነው፡፡ ከእኛ መስማት ብቻ ሳይሆን ከእርሱ የመናገር ችሎታ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪያችን ነው፡፡ የመረዳታችንንና የቋንቋ ችሎታችንን እንዴት እንደሚናገረን ያውቀዋል፡፡ በርሱ ደረጃ ሳይሆን በእኛ ደረጃ ወርዶ ነው የሚናገረን፡፡ ስለዚህ ፈቃዱን ለማድርግ እየወደድን እግዚአብሄን አንስተውም፡፡

ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።ዮሃንስ 7፡17

የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡       ዮሃንስ 10፡4 እኛ በጎች እንጂ ፍየሎች አይደለንም፡፡

·        ጆሮን ለሰይጣን መስጠት

ጆሮዋችንን ለሰይጣን ውሸትና ማስፈራሪያ ስንሰጥና ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ወሬ ስንሰማ ሰላማችን ይሰረቃል፡፡
በአለም ላይ መሰማት የሚመኙ ካልሰማሀን እያሉ የሚያስፈራሩ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ለነዛ ድምፆች ጆሮዋችንን ከሰጠን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡ ሁሌ ጆሮዋችንንና ልባችንን መስጠት ያለብን ለእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡  
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ኤርሚያስ 11፡4

በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ፊልጵስዩስ 4፡8-9

·        እግዚአብሄር ለእኛ ግድ እደሚለው አለማወቅ፡፡

ሰው ሁሉንም ነገር በራሱ እንዲሚያደርግ ሲሰማው ለማድረግ አቅሙ ስለሌለው ሰላሙ ይወሰዳል፡፡ እግዚአብሄር ስለእኛ ህይወት ግድ ይለዋል፡፡ እንዲያውም እግዚአብሄር ከምናስበው በላይ ስለ ዝርዝር የህይወት ጉዳያችን ይጠነቀቃል ግድም ይለዋል፡፡

እንዲያውም የእኛ ሃላፊነት ስለመንግስቱ ግድ መሰኘት ብቻ እንደሆነ እየሱስ ያስተምራል፡፡ ስለእኛ ግድ መሰኘትን  እግዚአብሄር የራሱ ስራ አድርጎ ወስዶታል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ እኛን መንከባከብ ያውቅበታል፡፡ እኛን በሚገባ ለመንከባከብ ምንም አስተማሪና አማካሪ አይፈልግም፡፡


ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።ማቴዎስ 6፡32-33

·        የአለም ከንቱ ውድድር

በአለም ውድድር ውስጥ ገብተን ከሚያስፈልገን መሰረታዊ ፍላጎት ውጭ መኖር ስንሞክር ሰላማችን ይወሰዳል፡፡

እግዚአብሄር ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን ከጎሮቤታችን እንድንበልጥ የሚያስችለንን ነገር አልሰጠንም፡፡ ወይም በአለም የቁሳቁስ (MATERIALISM) ውድድር ውስጥ ገብተን በምቾቶቻችን ለመክፈል የምንፈልገውን ስለማይሰጠንና እግዚአብሄር አብሮን ስለማይቆም በራሳችን ብቻ ስለምንፍጨረጨር ሰላማችንን እናጣለን፡፡

ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።ያዕቆብ 4፡3
መፅሃፍ ቅዱስ ህይወታችንነ ቀለል አድርገን ጌታን እንድናገለግልና ለሌሎች በረከት አንድንሆን ያስተምረናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህይወታችንን ከመራን በሰላም እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በምድር ላይ አድርገን እግዚአብሄርን እናከብራለን፡፡  


ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና።ምሳሌ 23፡4-5

አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቲዮስ 6፡8

·        እግዚአብሄር ለእኛ እንደሆነ አለማወቅ

እግዚአብሄር ሁሌ ለእኛ መልካምነት ይሰራል፡፡ ብንወድቅ እንኳን እንዴት እንደምንሳ ነው የሚያስበው  ተግቶም የሚሰራው፡፡
እግዚአብሄር ተቀብሎናል፡፡ እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ እንደተቀበለንና በእኛ ደስተኛ እንደሆነ ካላወቅን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡ እየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ እኛን ለመቀበል አርክቶታል፡፡

በእርግጥ በህይወታችን የማይወደው ነገር ካለ ያሳየናል፡፡ ከዚያ ውጭ እግዚአብሄር በእኛ በልጆቹ ደስተኛ ነው፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።2ኛ ቆሮንጦስ 5፡19

·        ትግስት ማጣት

ሌላው እየሱስ ሰላምን ሰጥቶን እያለ ሰላማችንን እንድናጣው የሚያደርገው ነገር የእግዚአብሄርን እርምጃ አለመታገስ ነው፡፡

እግዚአብሄር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ይሰጠናል፡፡ የሚሰጠን ግን በእኛ ጊዜ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገሮች በፍጥነት እንዲሆኑልን ስንምፈልግና የእግዚአብሄርን ፍጥነት ለመታገስ ራሳችንን ትሁት ካላረግንና በጌታ ላይ ካልተደገፍን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡

እግዚአብሄር አመጣጡ የዘገየ ቢመስልም ከእርሱ በላይ ፈጣን ስለሌለ የእግዚአብሄርን ላይ ብንደገፍ በሰላም እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ መታገስ ሰላማችንን እንዳናጣ ያስችለናል፡፡

2ኛ የጴጥሮስ 3፡9 ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥

·        ይቅር አለማለት

ሰላማችንን የሚሰርቅ ሌላው ነገር የበደሉንን ይቅር አለማለት ወይም በምህረት አለመመላለስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ኢነርጂ በተፈጠርንበት በፍቅርና በመልካም ስራ ላይ ከማፍሰስ ይልቅ ከሰይጣን ጋር ተባብረን በሰዎች ጥፋትና ክፋት ላይ እንድናፈሰው ስለሚያደርግ ሰላማችንን ይሰርቃል፡፡ ይቅር ማለት ቀላል አይደለም ነገር ግን ሁሌ ይቅር ማለት ይቻላል፡፡ ይቅር ማለት የስሜት ጉዳይ ሳይሆን የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ ይቅር ለማለት ከወሰንን በምህረት ለመመላለስ ራሳችንን ማስለመድ እንችላለን፡፡  

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንጦስ 10፡13 

እግዚአብሄር ባደረገልን ምህረትና ምን ይቅር ያለንን ስለሚያውቅ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ልንል የምንችልበት ብዙ የምህረት ካፒታል በቂ ጠቀማጭ እናዳለን ይተማመናል፡፡ ይቅር ማለት ከፈለግን እንደምንችል ያውቃል፡፡

ይቅር አለማለት ግን ከእግዚአበሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል፡፡ ይቅርታ ሰላማችንን እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡No comments:

Post a Comment