Popular Posts

Tuesday, November 22, 2016

አቤት ውሸት?

የጠላት ዲያቢሎስ አላማ ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት አይዘልም፡፡ ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሐንስ 10፡10
የህይወት ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያቢሎስ ከሚታወቅባቸው ስሞቹ አንዱ የውሸት አባት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሰይጣን ይዋሻል፡፡ ሰይጣን በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለተሸነፈና ስልጣኑን ስለአጣ አሁን የቀረው መሳሪያ መዋሸትና ማታለል ብቻ ነው፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሐንስ 8፡44
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3
ሰይጣን የሚዋሸው በእግዚአብሄር ቃል ላይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ከሌለ ሊያሳስተን ሁሌ ይመጣል፡፡ ሰዎች ይህን የሰይጣንን ውሸት ሲያምኑ በዚህም ህይወታቸው ሲበላሽ እናያለን፡፡ ሰይጣን እንዴት እንደሚዋሽ እንመልከት
  • · እየጠፋህ ነው ዋጋ የለህም ትወድቃለህ ካለህ የሰይጣን ማታለል መሆኑን አውቀህ በእግዚአብሄር ቃል ፀንተህ ተቃወመው፡፡ ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። ምሳሌ 4፡18
  • · ሰይጣን በሃጢያት ውስጥ ደስታ ይገኛል አለምህን ቅጭ እንጂ ለምን ጊዜ ያልፍብሃል? ካለ ሰይጣን እየዋሸህ ነው፡፡ በአለም የቀረብህ ነገር ቢኖር አሳፋሪ ፣ ፍሬቢስና መጨረሻው ሞት የሆነ ነገር ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። ሮሜ 6፡21
ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ዕብራውያን 11፡25-26
  • · ሃብታም የሆነው ሰው ሁሉ ሃብት ያገኘው በማጭበርበር ነው ካለ አንተም ካላጭበረበርክ መበልፀግ አትችልም ስለዚህ አጭበርብር እያለህ ነው፡፡ ይህ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰው በታማኝነት በእግዚአብሄር ሊበለፅግ ይችላል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
  • · እግዚአብሄር ለአንተ ግድ የለውም እራስህን አድን ፡፡ እግዚአብሄርን አትጠብቅ የራስህን መንገድ ሂድ የሚለው ድምፅ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰይጣን ሄዋንንም ተመሳሳይ ነገር ብሎዋት ነበር፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
  • · ማንንም አታገልግል ሰዎች ይጠቀሙብሃል ፡፡ ስለዚህ ከቤተክርስቲያን ሽሽ አምልጥ የሚልህ ሰይጣን ሲሆን ለምታገለግለው ለእግዚአብሄር ያለህን አመለካከት እያበላሸ ነው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ማቴዎስ 25፡24-26
  • · ሌላው ሰው አያስፈልግህም አንተ ብቻ በቂ ነህ ከአለህ ሰይጣን በትእቢት ሊጥልህ እያናገረህ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
  • · ካልተጨነቅህ ጤነኛ ሰው አይደለህም፡፡ አለመጨነቅ አይቻልም የሚለው የጠላት ድምፅ ነው፡፡ አንተ በቂ ጭንቀት አለህ እግዚአብሄርን ማምለክና ማገልገል የምትለውን ነገር ትተህ ለኑሮህ በመጨነቅ ህይወትህን ግፋ የሚለው ሰይጣን ዲያቢሎስ ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
  • · አንተ ምስኪን ነህ ለእግዚአብሄር የምትሰጠው ምንም ነገር የለህም የሚለው ሰይጣን ለብዙዎች በረከት እንዳትሆን ሊያደርግ ነው፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10
  • · ለማንም ቤተክርስቲያን አትገዛ ፣ በየትኛውም ስልጣን ስር አትሁን ፣ በግልህ ኑር አገልግል ካለህ ሰይጣን ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
  • · አንተ ብቻ ነህ በመከራ ውስጥ የምታልፈው ካለአንተ በስተቀር ሰው ሁሉ ኑሮ ቀሎለት እየኖረ ነው ካለህ ይህ ንግግር ከሰይጣን እንደሆነ እወቅበት፡፡ ሰይጣን ሁሉም ሰው ጋር እየሄደ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8-9
  • · አንተ በሃጢያት ከመውደቅ አልፈሃል ምንም መጠንቀቅ የለብህም ካለህ ይህ ሃሳብ ከሰይጣን ነው፡፡
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
  • · በእኔ ላይ የደረሰው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ነው፡፡ ከዚህ የምወጣበት ምንም መንገድ የለም ካልክ የሰይጣንን ንግግር አምነሃል ማለት ነው፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ውሸት #ሀሰት #ሰይጣን #ዲያቢሎስ #ጠላት #ማታለል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, November 20, 2016

ማን ጠራህ?

ለእግዚአብሄር መንግስት ስራ ተጠርተናል፡፡ ለእዚአብሄር ክብር ተጠጨርተናል፡፡ ጌታን የጌታን ህዝብ ለማገልገል ተጠርተናል፡፡ ለምን እንደተጠራን ማወቅ ለምን እንዳልተጠራን እንድናውቅ ያስችለናል፡፡ ለምን እንዳልተጠራን ካላወቅን እግዚአብሄር ለጥሪያችንን የሰጠንን ጉልበት ጊዜና ገንዘብ ሁሉ በተሳሳተ ቦታ ላይ አላግባብ እናባክነዋለን፡፡ ለምን እንዳልተጠራን ማወቅ ለምን እንደተጠራን ግልፅ እንዲሆንልንና ህይወታችንን በጥበብ እንድንመራ ያስችለናል፡፡
ለምን እንዳልተጠራን እንመልከት
  • · ከሌላው ጋር ለመወዳደር አልተጠራንም
ከሌላው ጋር ተወዳድርህ ያደረግከው ነገር ሁሉ ብክነት ነው፡፡ አንድ እንድትወዳደረው የተሰጠህ ደረጃ እግዚአብሄር የሰጠህ ራእይና ስራ ነው፡፡ የተሰጠህና ያለህ ለዚያ የሚበቃ ጉልበትና ፀጋ ብቻ ነው፡፡ ለሌላ ውድድር የሚበቃ ትርፍ ጊዜ ስለሌለህ ለውድድር የምታወጣው ወጪ ለራእይህ የተሰጠህን ወጪ ቀንሰህ ነው፡፡ በፉክክር የምታጠፋው ጉልበት የራስህን ጥሪ በሚገባ እንዳትፈፅመው ያግድሃል፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ገላትያ 6፡4-5
  • · ለሃሜት አልተጠራንም
ሰው የተጠራው ወንድሙን ሊደግፍና ሊያቀናው ነው፡፡ ወንድሙን በሆነ ባልሆነው የሚኮንን ሰው ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡ አንተ ህጉን መጠበቅ ህጉን እንዲጠብቅ ወንድምህን መርዳት እንጂ ወንድምን ማማት ከጉዳት ውጭ ምንም እንደማይጠቅምና ወንድምን ማማት ህጉን ራሱን ማማት እንደሆነ ያስተምራል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ መልእክት 4፡11
  • · ሰውን ለማሰናከል አልተጠራንም
በማንም ሰው ላይ የችግር ምክኒያት እንድንሆን አልተጠራንም፡፡ ሰውን ከመባረክና ከመጥቀም ውጭ ክርስትናን በማንም ላይ ከባድ እንድናደርግ አልተጠራንም፡፡ የሰውን ሸክም ለመሸከምና ሌላውን ለመባረክ እንጂ ማንንም ለማሰናከልና ለማሳዘን አልተጠራንም፡፡
ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር።ሉቃስ 17፡2
  • · ለቅናት አልተጠራንም
እንደ ልጅ እያንዳንዳችን ድርሻ አለን፡፡ እንደጥሪውና እንደተሰጠው ሃላፊነት የአንዱ ድርሻ ከሌላው ድርሻ ይለያል፡፡ የአንዱ የህይወት ተግዳሮት ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ የአንዱ ድርሻ ከሌላው ድርሻ ይለያያል፡፡ የአንዱ አቅራቦት ከሌላው አቅርቦት ጥሪው እንደሚጠይቀው ፍላጎት መጠን ይለያያል፡፡ ለጎረቤቴ ያልሰጠውን ስጦታ ከሰጠኝ ጎረቤቴ ያ ስጦታ የሚጠይቀው ተግዳሮት የለበትም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ለጎረቤቴን የሰጠውን ካልሰጠኝ እግዚአብሄር ይመስገን የጎረቤቴ ተግዳሮት የለብኝም ማለት ነው፡፡
ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡16
  • · ለመለያየት አልተጠራንም
ለመለያየት ከፈለግን የሚያለያዩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ትልቁ ነገር መለያየት ሳይሆን ትሁት ሆኖ በአንድ ሃሳብ መስማማትና አንዳችን ለአንዳችን መገዛት ነው፡፡ በትግስት ተቻችሎ ለአንድ አላማ መስራት እንጂ መለያየት ብዙ ጥረት አይጠይቅም፡፡ ትልቁ ነገር አብሮ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ለአንድ አላማ መስራት ነው፡፡
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2፡1-2
  • · ለማጉረምረም አልተጠራንም
እግዚአብሄር በግሉ የሚንከናከበው እንደኛ አይነት ህዝብ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ የሚያውቅ ፍፃሜና ተስፋ ያለው ሃሳብ ያለው እንደእኛ ማመስገንና ደስተኛ መሆን ያለበት ሰው የለም፡፡ ሁሉንም ለመልካም የሚለውጥለት እንደ እኛ አይነት ህዝብ የለም፡፡
በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ ፊልጵስዩስ 2፡14-15
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10
  • · ለጥላቻ አልተጠራንም
ይቅር ለማለት ለመፍታት ለመባረክ ለማንሳት ለመጥቀም እንጂ ማንም ሰው ለመጥላት አልተጠራንም፡፡ እግዚአብሄር እንደ እኛ ምህረት ያደረገለት ሰው የለም፡፡ ታላቅ ምህረት ያደረገልን እግዚአብሄር እኛም በተራችን ለሚበድሉን ሰዎች ምህረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል፡፡ ሰውን ይቅር እንዳንል ፣ በምሬት እንድንኖርና ሰውን እንድንጠላ አልተፈጠርንም፡፡
ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። ዘሌዋውያን 19፡17
ሌሎቹንም ያልጠራንን ነገሮች እርስዎም ይጨምሩበት
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥላቻ #ማጉረምረም #ቅናት #ሃሜት #ፉክክር #ማሰናከያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, November 18, 2016

ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው 12 ምርጥ ስጦታዎች

ገንዘብን ልኩን አለማወቅ በህይወት እንድንሳሳት የሚያደርገን ሲሆን ህይወታችንን በሙላት እንዳንደሰትበት ያደርጋል፡፡ እንዲያውም የሰው ብስለት ማወቂያው አንዱ መንገድ ለገንዘብ ያለውን ግምት በመመልከት ነው፡፡ ሰው ለገንዘብ ያለውን ግምት ከተበላሸ ለሌሎች ለሁሉም ነገሮች ያለው ግምት ይበላሻል፡፡
ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው በህይወታችን በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ እንዲያውም በህይወት በጣም ውዶችና ወሳኞቹ ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው በስጦታ የምናገኛቸው ነገሮች ናቸው፡፡
  • · ገንዘብ የትኛውንም የእግዚአብሄርን ስጦታ ሊገዛ አይችልም
ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ሐዋርያት 8፡20
  • · የትኛውም ያህል ገንዘብ እውነተኛን ፍቅር ሊገዛ አይችልም
ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 8፡7
  • · ብዙ ገንዘብ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ጤናማ ግንኙነትን እግዚአብሄርን መፍራትን ሊገዛ አይችልም፡፡
እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። ምሳሌ 15፡16
  • · ገንዘብ ለህይወት እጅግ የሚያስፈልገንን ጥበብን ሊገዛ አይችልም፡፡ አእምሮን የሚከፍት ማስተዋልን የሚሰጥ እግዚአብሄር ነው፡፡
በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ምሳሌ 17፡16
  • · የእምነት መስዋእትነት እንጂ የገንዘብ ብዛት የእግዚአብሄርን ሞገስ አይገዛም፡፡
አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው። ማርቆስ 12፡43-44
  • እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ በፍፁም እድልና ጊዜን አያገናኝም
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
  • · እግዚአብሄር እንጂ የትኛውንም ገንዘብ የልብህምን መሻት ሊሰጥህ አይችልም፡፡
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መዝሙር 37፡4
  • · ገንዘብ ሰላምን ሊገዛ አይችልም
የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። ምሳሌ 15፡17
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃንስ 14፡27
  • · እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም ማድረግ አይችልም
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
  • · በገንዘብ ብዛት ህይወት አይለካም
የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ሉቃስ 12፡15
  • · ምንም አይነት ገንዘብ ስራን ሊሰራ ይችላል እንጂ ክንውንን ሊሰጥ አይችልም
እኔም መልሼ፦። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው። ነህምያ 2፡20
ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። ዘሌዋውያን 26፡4
  • · ምንም አይነት ገንዘብ ለሰው ነፍስ ቤዛ ሊከፈል አይችልም፡፡
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ማቴዎስ 16፡26
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ገንዘብ #ብር #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የገንዘብ ሚስጥር

የገንዘብን ልክ አለማወቅ በህይወት እንድንሳሳት የሚያደርግና ህይወታችንን በሙላት እንዳንደሰትበት የሚያደርግ ነገር ነው፡፡ የሰውን ብስለት የሚለካው ሰው ለገንዘብ ያለውን ስፍራ በማየት ነው፡፡ ሰው ለገንዘብ ያለውን ግምት ከተበላሸ ሌሎች ነገሮች ያለው ሁሉ ግምት ይበላሻል፡፡
ሰው ገንዘብ ማድረግ የሚችለውንና ገንዘብ ማድረግ የማይችለውን ጠንቅቆ ካልተረዳ ከገንዘብ ጋር ያለው ግንኙነት ይበላሻል፡፡ ሰው ከልክ በላይ ለገንዘብ ክብር ከሰጠና ገንዘብን በህይወቱ መጀመሪያ ካደረገ ገንዘብን ይወዳል ይባላል፡፡
ገንዘብን መውደድ ወይም ከገንዘብ ጋር ያለ የተሳሳተ ግንኙነት ወይም ለገንዘብ ያለ የተሳሳተ ግምት ከሌሎች ነገሮች ጋር ያለ ግንኙነትን ሁሉ ያዛባል፡፡ ሰው ከገንዘብ ጋር ያለው ግንኙነት ከተሳሳተ ሌላ የማይሳሳት ምንም ግንኙነት አይኖረውም፡፡
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።1ኛ ጢሞቴዎስ 6:10
ገንዘብን የሚወድ ክቡሩን ሰውን አይወድም፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው እግዚአብሄርን ይጠላል፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው ገንዘብን ከሰው ያስበልጣል፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰውን መናቅ አይከብደውም፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው እግዚአብሄርን ለመውደድ አቅም ያጣል፡፡ ለገንዘብ የሚገዛ ለእግዚአብሄር መገዛት አይችልም፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
ገንዘብን የሚወድ ገንዘብን ስለማይጠግብ በህይወቱ የሚያጠግበውና የሚያረካው ምንም ነገር አይቀርለትም፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው ሰው ሊያረካው አይችልም፡፡ የሰው የህይወቱ አላማና ግብ እግዚአብሄርን መውደድና እግዚአብሄርን መፈለግ ነው፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው ግን የህይወቱ ብቸኛ ራእይና ግብ ገንዘብ ስለሚሆን ለእግዚአብሄር ጊዜ አይኖረውም፡፡ ገንዘብን የሚወድ ሰው በገንዘብ ፣ በሰውም ሆነ በእግዚአብሄር የመርካት እድሉን ጨርሷል፡፡
ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። መክብብ 5፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች
#ኢየሱስ #ጌታ #ገንዘብ #ብር #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ