Popular Posts

Sunday, June 19, 2022

ወዮልሽ! ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ

 

ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ! ንጉሥሽ የከበረ ልጅ የሆነ፥ ለብርታት እንጂ ለስካር ያይደለ በጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። መጽሐፈ መክብብ 10:16-17

ሰው በመሪነቱ የሚንፀባረቀው በህይወቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ የሰው የመሪነቱ ከፍታ ከህይወቱ ከፍታ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡

በሳልነት ለቤተሰብ ፣ ለቤተክርስትያን እንዲሁም ለሃገር መሪነት እጅግ ወሳዕ ነገር ነው፡፡ ንጉስሽ ህፃን የሆነ ብሎ የሚለው ስላላደገ ስላልበሰለ ሰው ነው፡፡ በየደረጃው ያለ መሪነት ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ሰው መሪ የሚሆነው በበሰለበት ደረጃ ብቻ ነው፡፡

የሰው በሳልነቱ የሚለካው ደግሞ በህይወቱ ዋጋ በሚሰጠው ነገር ነው፡፡ ሰው ለመብላት ለመጠጣት ለመዝናናት አልተፈጠረም፡፡ ሰው የተፈጠረው ለማገልገል ለመውደድ እና ለመጥቀም ነው፡፡ ሰው በህይወቱ ዋጋ የሚሰጠው ነገር መብላት መጠጣት መዝናናት ከሆነ በሳል ያልሆነ ያላደገ ሰው ነው ማለት ነው፡፡

ሰው ብስለቱ የሚለካው በህይወቱ ዋጋ በሚሰጠው ነገር ነው፡፡ ሰው ሁልጊዜ ስለ ፍቅር ፣ ስለ አገልግሎት እና ሌሎችን ስለመጥቀም የሚያስብ ከሆነ የበሰለ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ሰው ግን በመብላት ፣ በመጠጣት እንዲሁም ለራሱ መጠቀም ላይ የሚያተኩር ከሆነ የተፈጠረበትን አላማ በትክክል ያልተረዳ ያልበሰለ ሰው ነው ማለት ነው፡፡

ሰው በህይወቱ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ራሱን እንዲገዛ ያደርገዋል፡፡ ሰው በህይወቱ ዋጋ የሚሰጠውን ነገር በትክክል ሲያውቅ ለአገልግሎት እና ለፍቅር ሲባል ጊዜያዊ ደስታ ይቆይ ሊል ይችላል፡፡ ሰው በህይወቱ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ጊዜያዊ ሲሆን ራስ ወዳድ ስግብግብ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ንጉስሽ የከበረ ልጅ የሆነ የሚለው ጨዋን ራሱን የሚገዛ እና ጥንቁቅ የሆነን ሰው ነው፡፡ ሰው የሚከብረው እና የሚዋረደው ራሱን በሚይዝበት አያያዝ ነው፡፡ ሰው ራሱን በመልካም ባህሪ በሚገባ ከያዘ የከበረ ልጅ ይባላል፡፡

ረጋ ያለ በመልካም ባህሪ የከበረ ሰው ምልክቱ በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳቱ ነው፡፡ የከበረ ሰው ለመሰረታዊ ፍላጎት እንጂ ለቅንጦት ቅድሚያ አይሰጠም፡፡ ምግብ የሚበላውና የሚጠጣው እንኳን ራሱን ደስ ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል ለሰውነቱ ሃይል እና ብርታት ስለሚያስፈልገው ብቻ ነው፡፡ የሚበላው ገንዘብ እንዳለው ሃብታም እንደሆነ እንዲሰማው ሳይሆን ሰውነቱ ለመኖር ምግብ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡

የከበረ ሰው ስለራሱ ያለው አመለካት የከበረ እንደሆነ ነው፡፡ የከበረ ሰው ምን ያህል የከበረ እንደሆነ የራሱን ክብር በሚገባ ያውቀዋል፡፡ የከበረ ሰው ምግብ ስላልበላ ለራሱ ያለው አመለካከት አይቀንስም፡፡ የከበረ ጨዋ ሰው ምግብ ስላልበላ ድሃ እንደሆነ አይሰማውም፡፡ የከበረ ሰው ድሃ እንዳልሆነ እንዲሰማው ውድ ሆቴል ገብቶ ምግብ መብላት የለበትም፡፡ የከበረ ሰው ውድ መኪና ካልነዳ ከአለም ወደኋላ እንደቀረ አይሰማውም፡፡ የከበረ ሰው በራሱ ከመርካቱ የተነሳ ውድ ቤት ውስጥ ባይኖርም ምንም የሚቀንስበት ነገር እንደሌለ ያውቃል፡፡

በተቃራኒው ያልከበረ ሰው የህዝብ መሪ መሳፍንት ሲሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ህዝቡን በትጋት ማገልገል ሳይሆን ራሱን በቅድሚያ ማስደሰት ነው፡፡ ያልከበረ ሰው በህይወቱ እርካታ ስለሌለው እርካታን የሚፈልገው ከምግብ እና ከመጠጥ ነው፡፡ ያልከበረ ሰው ደስታ ስለሌለው በስካር ራሱን በማደንዘዝ ላይ ያተኩራል፡፡ ያልከበረ ሰው በስሩ ያሉት ብዘዙ ህዝቦች እንዴት እንደሚለወጡ ከማቀድና በትጋት ለመከናወናቸው ከመስራት ይልቅ በአንድ ራሱ ሃሳብ ላይ ተጠምዶ ይኖራል፡፡   

ሌሎች መድረስ የምንችለው እና ሌሎችን ማገልገል የምንችለው ያለኝ ይበቃኛል ባልንበት የህይወት አቅጣጫችን ብቻ ነው፡፡

ህፃን የሆነ ሰው ሲመራ ህዝቡን እግዚአብሄር ወደአየላቸው ቦታ ማድረስ አይችልም እንዲሁም ራስን ስለመካድ ለህዝቡ መልካም ምሳሌ ሊሆናቸው አይችልም፡፡ የብዙ ህዝብን ፍፃሜ የመለወጥ እምቅ ጉልበቱን እና እድሉን በአንድ በራሱ ላይ ብቻ ያባክነዋል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ልጅነት #ብርሃን #ጨው #ምስክርነት #ጌታክርስቶስ #ርስት #ብድራት #ስራ #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለጠግነትምቾት #አቅርቦት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment