Popular Posts

Monday, September 7, 2020

ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም። ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም። ትንቢተ ዳንኤል 4:34-35

 


የደቦ ይቅርታ

 


በአገራችን ጳጉሜ 1 የይቅርታ ቀን ተብሎ ታውጆዋል፡፡ ይቅርታ ደግሞ ብዙ በረከቶችን የተሸከመ ድንቅ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ልምምድ ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የመፅሃፍ ቅዱስ መርህ የሚባርከን እንደሃይማኖት ስርአት ሳይሆን ተረድተነው ስንለማመደው ብቻ ነው፡፡

እንደው እንደ ሃይማኖት ወግ የምናደርገው ነገር በህይወታችን የታለመለትን አላማ እና ግብ ሊመታ አይችልም፡፡ እንደው ሌላው ሰው ስላደረገው ብቻ የምናደርገው ሃይማኖታዊ ልምምድ ሊባርከን አይችልም፡፡ እንደው ከዚህ የይቅርታ በረከት እጎድላለሁ ብሎ በመፍራት ብቻ እንደ ሃይማኖታዊ ወግ የምናደርገው ነገር እውነተኛውን ይቅርታ እንዳንለማመድ ራሳችንን ያታልለናል እንጂ የሚጠቅመን ነገር አይኖርም፡፡  

እግዚአብሄር የፈጠረን ተባብረን ለአንድ አላማ እንድንሰራ እና አንዳችን አንዳችንን እንድንባርክ ነው፡፡

ይቅርታ ደግሞ በሁለት ሰዎች መካከል የነበረን የአንድነትና የትብብር ግንኙነት መበላሸት የምናስተካክልበት መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ነው፡፡

ይቅርታ መጠየቅ በደቦ የማይሰራና በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡

ሰውን እንደበደልነው ስናውቅ ይቅርታ ወደ በደልነው ሰው ሔደን መጠየቅ አለብን፡፡ ይቅርታ ስንጠይቅ እንደው ይቅርታ ብቻ ለመጠየቅ ሳይሆን ይቅርታ ከጠየቅንበት መንገዳችን ለመመለስ ነው፡፡ ይቅርታ ስንጠይቅ ተሳስቻለሁ ከዚህ በኋላ አላደርገውም እያልን ለበደልነው ሰው ቃል እየገባን ነው፡፡

የበደለን ሰው ወደእኛ መጥቶ ይቅርታ ሲጠይቀን ደግሞ ይቅር ማለት አለብን፡፡

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። የማቴዎስ ወንጌል 18፡21-22

ሳላውቅ በስህተት ሚለው የደቦ ይቅርታ አጠያየቅ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አውቀን ስላልሰራነው ነገር እንጠየቃለን ብዬ አላምንም፡፡ አውቀን ስላለሰራነው ነገር እልፍ ጊዜ ይቅርታ ብንጠይቅ ስህተታችንን ስለማናውቅው ተመልሰን እንዳማናደርገው ማረጋገጫ የለውም፡፡

ሰውን መበደላችንን እርግጠኛ ካልሆንን ወደ ሰውየው ሔደን መነጋገር መፅሃፍ ቅዱሳዊ ግንኙነትን የማስተካከያ መንገድ ነው፡፡

እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡23-24

ስህተት እንደሰራን እርግጠኛ ባልሆነው ነገር ሳላውቅ በስህተት ብሎ በደፈናው ማለፍ ከእውነተኛው መፅሃፍ ቅዱሳዊ በረከት ያጎድለናል፡፡ እንዲሁም ስህተት እንደሰራን ለማረጋገጥ ሔደን ባልተነጋገርነው ነገር ሳላውቅ በስህተት ብሎ በደፈናው ማለፍ እውነተኛውን መፅሃፍ ቅዱሳዊ በረከት ሊያስገኝልን አይችልም፡፡  

በየትኛውም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል ማንም ሰው ሳላውቅ በስህተት የሰራሁትን ይቅር በለኝ በሚለው መርህ ይቅርታ ሲጠይቅም ሆነ ሌሎች ይቅርታ እንዲጠይቁ ሲተያስተምር አይቼ አላውቅም፡፡  

ሳላውቅ በስህተት ተብሎ የሚጠየቅ ይቅርታ ባዶ ሃይማኖታዊ ወግ እንጂ ምንም አይነት መፅሃፍ ቅዱሳዊ መሰረት እና ጥቅም የሌለው የሰው ስርአት ነው፡፡

ራሳችንን ትሁት አድርገን ወደ በደልነው ሰው ሔደን ወይም ደውለን ይቅርታ ከመጠየው ይልቅ እንዲሁም በጅምላ የበደልኩዋችሁ ሁሉ ይቅር በሉኝ ማለት ከዋናው የመፅሃፍ ቅዱስ በረከት የሚያጎድለን መንፈሳዊ የሚመስል ባዶ ሃይማኖታዊ ወግ ብቻ ነው፡፡ በጅምላ ይቅርታ ከምንጠይቀው ህዝብ ይልቅ የበደልነውን ሶስት ሰው በግል ይቅርታ መጠየቅ ህይወታችንን ይለውጠዋል፡፡ ካልበደልክና ወይም በደልህን ካልተረዳኸው እግዚአብሄርም ሰውም አይፈርድብህም፡፡ የምትጠየቀው ስለምታውቀው ብቻ ነው፡፡ ከበረከት ላለመጉደል እንደ አጠቃላይ ምርመራ የምታደርገው የይቅር በሉኝ ጥሪ ከፍርሃት እንጂ ከእምነት አይደለም፡፡ አትፍራ ካልበደልክ ወይም በደልህን ካልተረዳኸው ከየትኛውም የእግዚአብሄር በረከት አትጎድልም፡፡  

መልካም የይቅርታ ቀን ! መልካም የይቅርታ ወር ! መልካም የይቅርታ አመት !

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ይቅርታ #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ምህረት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

Sunday, September 6, 2020

ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ትንቢተ ሚክያስ 6:8

 


ህይወት ልንደሰትበት የሚገባ የእግዚአብሄር ስጦታ

 


ህይወት ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ የተፈጠርንበትን አላማ ለመኖር ትልቅ  ትጋት ይጠይቃል፡፡ ህይወት ጥንቃቄን የሚጠይቅ የቤት ስራ ነው፡፡ ህይወት ትልቅ ሃላፊነትን የሚጠይቅ ሸክም ነው፡፡

ህይወት ደግሞ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ህይወት ሸክም ብቻ ሳይሆን ልንደሰትበት የሚገባ የእግዚአብሄር በረከት ነው፡፡ በህይወት በመኖራችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ የእግዚአብሄርን ስራ በመስራታችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እግዚአብሄርን በመፍራታችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ለእግዚአብሄር መንግስት ዋጋ በመክፈላችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እግዚአብሄር እምላካችን ስለሆን ልንደሰት ይገባል፡፡  ለእግዚአብሄር ነገር ታማኝ በመሆናችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ለእግዚአብሄር ስራ በመትጋታችን ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ካለፍርሃት በደስታ እንድናገለግለው ሰጥቶናል፡፡ 

በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። የሉቃስ ወንጌል 174-75

ሰይጣን እንደሆነ የሚለው ምንም ነገራችን በቂ አይደለም ነው፡፡ ለሰይጣን ምንም ነገራችን አያምረውም፡፡ የሰይጣን አላማ እኛን ማሰናከል ስለሆነ ለሰይጣን ምንም ነገራችን አበቃውም፡፡ ለሰይጣን ምንም ነገራችን አይጥመውም፡፡ የሰይጣንን ነገር እየሰማን በላያችን ላይ ልንከፋ አይገባም፡፡

እግዚአብሄር ደግሞ ከእኛ ብዙ ነገር አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው በመጨረሻ እንድምንጠየቅ አድርገን ብቻ እንድንወጣና ህይወታችንን በደስታ እንድንኖር ብቻ ነው፡፡

የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና። መጽሐፈ መክብብ 1213-14

እግዚአብሄር እንድንደክም ብቻ ሳይሆን በድካማችን ደስ እንዲለን ይፈልጋል፡፡ ህይወት ሸክም ብቻ ሳይሆን ስጦታ መሆኑን አውቀን እንድንደሰትበት የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡

ህይወትን እንደሸክም ብቻ በሚያየው ሰው እና እንደስጦታ በማይደሰትበት ሰው እግዚአብሄር አይደሰትበትም፡፡ ህይወትን እንደሸክም ብቻ የሚያየው ሰው እና እንደስጦታ የማይደሰትበት ሰው በህይወቱ ስኬታማ አይሆንም፡፡ ህይወትን እንደሸክም ብቻ የሚያየው ሰው እና እንደስጦታ የማይደሰትበት ሰው በሚዛናዊነት ስላልያዘው ብዙም አይዘልቅም፡፡

ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን፦ እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ የሉቃስ ወንጌል 1528-29

የአባቱ መልስ ግን ለእኔ ለአባትህ መኖር በአባትህ እንዳትደሰት ሊያደርግህ አይገባም ነበር የሚል መልዕክት ያለው ነበር፡፡

እርሱ ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል 1531

እግዚአብሄር ሲባርክ የሚባርከው በትጋትና በደስታ ነው፡፡ ደስታ የሌለው ትጋት አሰቃቂ ነው፡፡ የህይወትን ሸክም የሚያቀለው የልባችን ደስታ ነው፡፡

እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር በልቡ ደስታን ስለ ሰጠው እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግ አያስብም። መጽሐፈ መክብብ 518-20

ዛሬ አሁን ባለንበት በዚሁ በደረስንበት ደረጃ በእግዚአብሄር ስጦታ በህይወት መደሰት ካልቻልን የሆነ ያልገባን ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ህይወት ሸክም ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን ደረጃና ዝርዝር ልንደሰትበት የሚገባ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡

ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 815

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #መደሰት #ስኬት #ህይወት #ስጦታ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #ሃዋርያውአቢይ #አቢይዋቁማ #ሃዋርያውአቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #ማስተዳደር #እረፍት

Thursday, September 3, 2020

የተሸነቆረ ሸክላ

 


እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት አምነን የዳንን ሁላችን እግዚአብሄር በምድር ላይ ለሰጠን የቤት ስራ በእግዚአብሄር መንፈስ ተቀብተናል፡፡ ካለ እግዚአብሄር መንፈስ እርዳታ  የእግዚአብሄርን ስራ መስራት አይቻልም፡፡ የእግዚአብሄር አላማ በምድር ላይ መፈፀም ካለበት የእግዚአብሄር መንፈስ አብሮን ሊሰራ ይገባዋል፡፡

በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡21

ታዲያ ችግሩ ቅባቱን ጠብቆ ለሚፈለገው አላማ ማዋል እንጂ መቀባቱ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ብንቀባ ቅባቱን በመልካም የእግዚአብሄራዊ ባህሪ ጠብቀን ካላቆየነው ለታለመለት አላማ ሊውል አይችልም፡፡

የቅባቱ መያዣ ሸክላው በባህሪ ጉድለት የተሸነቆረና በክርስቶስ ባህሪ ካልተጠበቀ በስተቀር ቅባቱን ያባክነዋል፡፡

እግዚአብሄር ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት እኛን መቀባት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት የተቀባነውን ቅባት ለረጅም ጊዜ አቆይተን ለታለመለት አላማ ሁሉ መጠቀም እንድንችል የቅባቱን መያዣ ሸክላውን መስራት ነው፡፡ እኛን መቀባት ለእግዚአብሄር የሰከንድ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን  የቅባቱን አስተዳዳሪ እኛን እግዚአብሄርን በመምሰል መስራት ግን የብዙ ጊዜ ስራ ነው፡፡

ህይወታችን ትእግስት ፣ የዋህነት እና ፍቅር ከጎደለው የተቀባነውን ቅባት ለታለመለት አላማ ሳይውል እናባክነዋለን፡፡

ስለዚህ ነው ቅባት ወደከፍታ ይወስድሃል ባህሪ በከፍታው ላይ ይጠብቅሃል የሚባለው፡፡

ብዙ ሰዎች ግን ስለመቀባታቸው ሃይል ስለማግኘታቸው እንጂ ሃይሉን ለረጅም ጊዜ ስለሚያቆየው ስለባህሪያቸው አያስቡም፡፡ እኛ መቀባት ከምንፈልገው በላይ እኛ እንድንቀባ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የእኛ ድርሻ ቅባቱን ለረጅም ጊዜ እና ለታለመለት አላማ ሁሉ ለመጠቀም የሚያስችለንን የቅባቱን መያዣ ባህሪያችንን በእግዚአብሄር ቃል ለመስራት እንትጋ፡፡

 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #ቅባት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ሃይል #ሰላም #ደስታ #ሃዋርያውአቢይ #ሃዋርያውአቢይዋቁማ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #የዋህነት #ትግስት #መሪ

Wednesday, September 2, 2020

ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፤ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል። መዝሙረ ዳዊት 30፡5


 ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፤

ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።
መዝሙረ ዳዊት 30፡5