Popular Posts

Friday, August 30, 2019

የፍሬ ፍሬ


ለፍሬያማነት መተከልና ስር መስደድ ወሳኝ ነው፡፡ የትኛውም ዘር ስር ሳይሰድ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ዘር ፍሬ ለማፍራት መጀመሪያ ከምንጩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል፡፡ ዘር አድጎ ፍሬ ከማፍራቱ በፊት ፍሬ ሊያፈራ ከሚያስችለው አቅራቦት ጋር በሚገባ መገናኘት አይችልም፡፡
እድገቱ አስተማማኝ እንዲሆን ተክል ስር መስደድ አለበት፡፡ ተክል እንዲያድግና እንዲፈራ ክር መስደድ ወሳኝ ነው፡፡ አንድ ተክል ሊያድግና ፍሬ ሊያፈራ የሚችለውስር በሰደደው መጠን ብቻ ነው፡፡
በክርስትናም ለማደግና ፍሬ ለማፍራት ለማደግ ከሚያስፈልገው ከእግዚአብሄር ቃል ጋር በሚገባ መገናኘት ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ሳይዙ ለማደግ እና በህይወት ፍሬ ለማፍራተ መሞከር መሰረት ሳይሰሩ ቤት ለመስራት እንደመሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡
ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። የማቴዎስ ወንጌል 7፡26-27
ስር ካልሰደደ ተክል እድገትና ፍያማነት መጠበቅ ከንቱ እንደሆነው ሁሉ በእግዚአብሄር ቃል ልምምድ ስር ካልሰደደ ክርስትያን መንፈሳዊ እድገትና ፍሬያማነት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡  
ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥7
ስርና መሰረታቸው በእግዚአብሄር ቃል በጌታ ያልፀኑ ሰዎች የማይያዙ የማይጨበጡ በጠንካራ መሰረት ላይ ያልታነፁ ሰዎች ናቸው፡፡  
እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡14
በአንዴ የሚያፈራ ተክል እንደሌለ ሁሉ ለማፍራት መቆየት እና መኖር ይጠይቃል፡፡ ለማፍራት ራስን በመስጠት መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ ለማፍራት ራስን በመስጠት መቆየት መኖር ይጠይቃል፡ 
በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። የዮሐንስ ወንጌል 15፡4
በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። የሉቃስ ወንጌል 8፡15
ምንም ግንኙነት ካለመቆየት ፍሬ አይሰጥም፡፡ የተክሉና ለተክሉ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በስሩ አማካኝነት ካልተገናኘ ተክሉ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ቦታ የሚተከል ችግኝ መጠውለጉና ለፍሬ ሳይበቃ መድረቁ አይርም፡፡  
በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፥16-17
እግዚአብሄርን የምናስከብረው በፍሬ ብቻ ነው፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። የዮሐንስ ወንጌል 157-8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ሬያማነት #ፍሬ #ስር #መሰረት #ማፍራት #ስኬት #በእኔኑሩ #ቃል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መመዘኛ #መስፈርት #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, August 21, 2019

ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?



እግዚአብሄር ምንም ያህል መንገዱን እንድንከተል ቢፈልግም ነገር ግን የእግዚአብሄርን አላማ መሳት አለ፡፡ እግዚአብሄር ምንም ያህል እንዳንስት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ቢያዘጋጅም ነገር ግን መሳት በህይወታችን ይከሰታል፡፡ መሳት የማይያዝ የማይጨበጥ ሃይማኖታዊ ሃሳብ ሳይሆን እውን በእለት ተእለት ህይወታችን ሊከሰት የሚችል ክስተት ነው፡፡
በህይወታቸው የእግዚአብሄርን መንገድ የሚጠብቁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በህይወታቸው የእግዚአብሄርን መንገድን የሚስቱ ሰዎች አሉ፡፡ በህይወታቸው መሄድ የማይፈልጉበት ቦታ ራሳቸውን የሚያገኙ ሰዎች አሉ፡፡
እኛ የእግዚአብሄርን መንገድ መሳት ከማንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እንዳንስት ቢፈልግም ነገር ግን መሳት በሰው ልጆች ህይወት ላይ የሚከሰት ያለ ነገር ነው፡፡ መንገዱን እንዳንስት እግዚአብሄር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ቢያዘጋጅም እንኳን መሳት እውን ነው፡፡ መንገዱን እንዳንስት እግዚአብሄር ካዘጋጃቸው እጅግ ብዙ ነገሮች አንፃር መሳት ከባድ ቢሆንም ነገር ግን እግዚአብሄርን መንገድ ልንስት አንችለም ማለት ግን በፍፁም አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር ፍቅር አንፃር ለሰው ከመሳት ይልቅ አለመሳት ቢቀለውም ነገር ግን መሳት የለም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን እየፈለግን መሳት ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ካልተጠነቀቅን ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 7፡17
ልስት አልችልም ብለን ስላሰብን ብቻ አንስትም ማለት አይደለም፡፡ ከሚስቱ ሰዎች አብዛኛዎቹ ከመሳሳታቸው በፊት መሳት የሚባለው ነገር እኔ ላይ ላይ አይደርስም ብለው አስበዋል፡፡ የማይጠነቀቀውና የሚስተው ልስት አልችልም ብሎ የሚይስብ ሰው ብቻ ነው፡፡  
ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ” ያድንሃል። መጽሐፈ ምሳሌ 2:11
እኛም ብዙ ጊዜ ለዚህ አሳልፈ አልሰጥም ብለን ላሰብንለት ነገር ተሰጥተን ራሳችንን አግኝተነዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ በእኔ ላይ አይሆንም ብለን ያሰብነው ነገር ሆኖብን አይተናል፡፡
ምንም ያህል ነገሮች የምናይና የምናውቅ ብንሆን የማናያቸው ነገሮች አሉ ብለን ማሰብ እና የእግዚአብሄርን እርዳታ በቀጣይነት መፈለግ ጥበብ ነው፡፡  
የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል። መጽሐፈ ምሳሌ 21፡2
ጌታ  ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል ባለ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ እኔ እሆንን? ይሉ ጀመር፡፡
ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። የማቴዎስ ወንጌል 26፡21-22
ማነው እርሱ አሳልፎ የሚሰጥህ ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እኔ እሆንን ማለት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እርሱ ማነው የሚለው ብቻ ሳይሆን እኔ እሆንን ማለት ትህትና ነው፡፡ አንተ አይደለህም ብሎ ሊመሰክር የሚችል የእግዚአብሄር ቃልና የእግዚአብሄር መንፈስ ብቻ እንጂ እኛ ራሳችን አይደለንም፡፡  ወደድንም ጠላንም አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ውስጥ ያለው ስጋ እኛም ውስጥ ይኖራል፡፡ ይሁዳን ያሳሳተው ሰይጣን እኔን ሊያሳስተኝ አይችልም ብሎ አለመጠንቀቅ በእርግጥ መሳትን ያስከትላል፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋርያው ፍራ እንጂ የትቢትን ነገር አታስብ ያለው ለዚህ ነው፡፡ የሚወድቁት ልወድቅ አልችልም ብለው የማይጠነቀቁ ሰዎች ናቸው፡፡ የሚወድቅ ሰው ምልክቱ ልወድቅ አልችልም ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ አንተ ልትወድቅ እስከማትችል ድረስ መጠንቀቅ የለብህም ብሎ ካሳመናችሁ ሰይጣን እንጂ እግዚአብሄር ሊሆን ፈፅሞ አይችልም፡፡  
መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። ወደ ሮሜ ሰዎች 11፡20
ታላቁ ሃዋርያው ጳውሎስ እንዳይስትና እስከመጨረሻው ፀንቶ ለመቆም የሚያደርገውን ጥንቃቄ እያየን እኔ አልስትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #መንገድ #ድምፅ #ጌታ #መሳት #ስህተት #ትእቢት #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጥንቃቄ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, August 19, 2019

መንገድህን እባክህ አሳየኝ


አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። ኦሪት ዘጸአት 33፡13
መንገድህን እባክህ አሳየኝ ልመና ከእግዚአብሄር መንገድ ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ አደገኛ የሆነ የብክነት ህይወት እንደሆነ የተረዳ ሰው የልብ ጩኸት ነው፡፡
አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ። መዝሙረ ዳዊት 25፡4
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት ህይወቱን ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጭ ላማባከን የማይፈልግ ሰው የልብ ጩኸት ነው፡፡
አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።  መዝሙረ ዳዊት 86፡11
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት በእግዚአብሄር መንገድ ብቻ እውነተኛ ስኬት ፍሬማነትና ውጤት እንደሚገኝ የተረዳ ሰው የልብ ጩሸት ነው፡፡
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት ለእያንዳንዳችን የተወሰነ የተለየ መንገድ እንዳለ ሰው ስለሄደበት ብቻ በግርታ መሄድ እንደሌለበት የተረዳ ሰው የልብ ጩኸት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት እኛ እንዲመራን ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር ሊመራን እንደሚፈልግ የተረዳ ሰው የልብ ጩኸት ነው፡፡
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት ከእግዚአብሄር መንገድ ውጭ የሆነው የእኛ መንገድ የትም የማያደረስ የድካምና እና የከንቱነት መንገድ እንደሆነ የተረዳ ሰው ጩኸት ነው፡፡
መንገድህን እባክህ አሳየኝ የሚለው ጩኸት ለመሄድ ብቻ ብሎ እግዚአብሄር በሌለበት መንገድ ከመሄድ አለመሄድ መቅረት እንደሚሻል የተረዳ ሰው የልብ ጩኸት ነው፡፡
እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። ኦሪት ዘጸአት 33፡15
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #መንገድ #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, August 17, 2019

በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ


እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16 

ክርስትና የሚቻለው በእግዚአብሄር እርዳታ ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር እርዳታ ውጭ እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻለም፡፡ እግዚአብሄር በሚያስችል ፀጋው ካላስቻለን ፈቃዱን አድርገን እግዚአብሄርን የሚያስደስት ህይወት ሊኖረን አይችልም፡፡ 

ለእግዚአብሄር መኖር እየፈለግን አንዳንድ ጊዜ አቅም እናጣለን ይደክመናል፡፡ ለእግዚአብሄር እንዴት መኖር እንዳለብን እናውቃለን ነገር ግን ጉልበት እንደከዳን ይሰማናል፡፡ በየት መንገድ መሄድ እንዳለብን እናውቃለን ነገር ግን ተጨማሪ እርምጃ ለመራመድ ጉልበት እንዳነሰን ይሰማናል፡፡ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንፈልጋለን ነገር ግን ከተለያየ ምክኒያት የተነሳ ይታክተናል እርዳታን እንፈልጋለን፡፡ 

ለጌታ ለመኖር ፈቃዱን ለማድረግና በነገር ሁሉ እርሱን ለማስደሰት ያለን ብቸኛ አማራጭ ወደ እርሱ መሮጥ ነው፡፡ በኑሮዋችን እርሱን ማስደሰት የምንችልበትን በሚያስፈልገን በትክለኛው ጉልበት የምናገኘው ከፀጋው ዙፋን ነው፡፡ 

የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ ሁልጊዜ ሊረዳ ሊደግፍ ፈቃደኛና የተዘጋጀ መልካም አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ እርዳታውን የሚፈልጉትን በመርዳት የተካነ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት በህይወታችን የሚገጥመንን ማንኛውንም ተግዳሮት ለማለፍ የሚያስችል ብቃትን የምናገኘው ከእርሱ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዙፋን የፀጋው ዙፋን የተባለበት ምክኒያት እርሱ ከልባቸው እርዳታውን የሚፈልጉትን ለመርዳት አይኖቹ በምድር ላይ ስለሚመላለሱ ነው፡፡ 

እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 16፡9 

የእግዚአብሄርን ፈቃድ ላለማድረግ ምንም ሰበብ የለንም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችለንን ፀጋ እንድንቀበል ወደፀጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ፡፡ ይበልጥ ወደ ፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን ይገለጣል፡፡ ይበልጥ ወደፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ በድካማችን ላይ የእግዚአብሄር ፀጋ ብርታት ይገለጥበታል፡፡ ይበልጥ ወደፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ የእግዚአብሄር ፀጋ ድካማችንን ይሸፍናል፡፡ ይበልጥ ወደ ፀጋው ዙፋን በቀረብን መጠን ይበልጥ ድካማችን በብርታት ይለወጣል ለእግዚአብሄርም ለመኖር አቅም እናገኛለን፡፡ 

ወደ ፀጋው ዙፋን መቅረብ ያለብን ደግሞ በእምነት ነው፡፡ ስለአንድ የህይወታችን ጥያቄ ወደፀጋው ዙፋን ከቀረብን በኃላ እግዚአብሄር የሚያስችለውን ፀጋ እንደሰጠን አምነን መሰማራት አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ እንደተቀበልን የምናውቀው በእምነት እንጂ ወደ ፀጋው ዙፋን እንደቀረብን እየበረረ መጥቶ የሚገባብን በተፈጥሮአዊ አይን የሚታየ ፀጋ የለም፡፡ እግዚአብሄር ሊደግፈን እንደሚፈልግ በማመን ወደፀጋው ዙፋን ከቀረብን በኃላ ታምነን መሰማራት አለብን፡፡ 

በእግዚአብሔር ታመን፥ . . . ታምነህም ተሰማራ። የዳዊት መዝሙር። 37፡3 

እንደፈቃዱ እንደፀለይን ካመንን እንደተቀበልን እናውቃለን፡፡ 

በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፡14-15 

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ 

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes 

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos 

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #የሚረዳንን #ፀሎት #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ.