Popular Posts

Sunday, October 2, 2022

ርህራሔ የሌለበት የኢሬቻ አስተያየት

 

ርህራሔ የሌለበት የኢሬቻ አስተያየት
ሰሞኑን የኢሬቻ በአል እየተከበረ ይገኛል:: ስለ ኢሬቻ በአል ብዙ አይነት አስተያየቶችን ሰምቻለሁ እንብቤያለው::
አንድ የታዘብኩት ነገር ግን የኢሬቻን በአል ተቃውመው የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች ፍቅርና ትህትና በጎደለው ሁኔታ የበአሉን ታዳሚዎች ሲወቅሱ ማየቴ ነው፡፡  
በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3:15
የበፊቱን አላውቅም በአሁኑ ዘመን ከማየው ስነሳ የኢሬቻ በአል ከሀይማኖትነቱ ይልቅ ብሔራዊ ባህልነቱ ያመዝንብኛ፡፡ 
ሀይማኖት ቢኖረንም ባህልም ያለን ባህላዊ ሰዎች ነን:: ሃይማኖትን በማይነካ መልኩ የምናስተናግዳቸው ብዙ ባህሎች አሉን፡፡ ባህል በሃይማኖታችን ላይ ምንም ያህል ተፅእኖ እንዳያደርግ እና የሀይማኖት ህይወታችንን እንዳያዘገይ ወይም እንዳያቆም በኑሮዋችን መጠንቀቅ የእለት ተእለት ሃላፊነታችን ነው:: 
ማንኛውም ባህል እምነታችንን የሚቃወም ከሆነ የትኛውንም ባህል አውጥተን እንጥላለን እንተወዋለን:: ስለ እምነታችን ከእግዚአሔር ቃል ጋር ከማይሄድውን ባህላችንን በደስታ እንተዋለን:: 
እኔን በተመለከተ ስለሀጢያቴ በመስቀል ላይ የሞተውን ሞትን ድል አድርጎ በሶስተኛው ቀን የተነሳውን ኢየሱን ክርስቶስን አዳኝና ጌታ አድርጌ እከተላለው:: ኢየሱስን ለማይከተል ሰው ከዚህ ታላቅ በረከት ስለጎደለ በቅንነት አዝንለታለሁ:: 
ነገር ግን የኢሬቻን በአል በሚያከብር ሰው ላይ ላለመፍረድ እጠነቀቃለው:: የምናገረው ንግግር የዋህነትና ትህትናን ካጣ ከጥቅሙ በላይ ጉዳቱ ያመዝናል:: በፍቅር ያልተደረገ ነገር ከንቱ ነው ምንም አይጠቅምም:: 
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ቆሮንጦስ 13:1-3 
የማንወደውን ሰው ልናገለግለው እንችልም:: እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆነ ባህል እምነታችንን እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ፣ ሌሎችን በየዋህነት እና በትህትና መምከር እንጂ ርህራሔ ያጣ አስተያየት መስጠት ምንም ለምንም አይጠቅምም::
 በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3:15
አቢይ ዋቁማዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment