እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ የፈጠረን እግዚአብሄር በህይወታችን ምን እንደምንሰራ ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር ምን እንደምንሰራ ግድ እንደሚለው ሁሉ ለምን ምክኒያት እንደምንሰራው ደግሞ ግድ ይለዋል፡፡
አንድን ነገር ለማድረግ ያነሳሳን ነገር በተለይም የተደበቀ ወይም ግልጽ ያልሆነ
ምክንያት ተነሳሽነት /motive/ ይባላል። ታዲያ የምንሰራውን ነገር ከምንም የልብ መነሻ ሃሳብ ወይም ተነሳሽነት
/motive/ እንደሆነ እግዚአብሄር ማወቅ ይፈልጋል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ምንም መልካም ነገር ብናደርግ ከፍቅር መነሻ ሃሳብ ካላደረግነው ከንቱ
እንደሆነ እና ምንም እንደማይጠቅመን ያስተምረናል፡፡ ልብን የሚመዝነው እግዚአብሄር የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን በምን መነሻ
ሃሳብ እንደምናደርገው ያያል፡፡ እግዚአብሄር እንድን መልካም ነገርን ስላደርግን ብቻ ጎሽ አይለንም ወይም ደስ አይሰኝም፡፡ በፍቅር
ወይም በራስ ወዳድነት ለግል ስማችን ብለን ወይም በፉክክር ስሜት እንዳደረግነው የሰውን ልብ የሚመዝነው እግዚአብሄር ያውቃል፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ
ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ
ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡2-3
መልካሙን ነገር በፍቅር ካላደረግከው እና በጥላቻ ወይም በፉክክር ካደረግከው ተራሮችን
በእምነት ስናፈልስ ወንድማችንን ለመጉዳት የወንድማችን መንገድ ለመዝጋት ልናደርገው እንችላለን፡፡
እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ
በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡2
በምታደርገው ነገር ልትረካ ሰውንም ልታስደንቅ ትችላለን እግዚአብሄርን ግን በተበላሸ
የልብ መነሻ ሃሳብ ባደረግከው ነገር ልታታልለው ወይም ልታስደንቀው አትችልም፡፡
ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን
ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡5
ስለዚህ መልካምም ነገር ቢሆን እንኳን የምናደርገው ነገር በምን የልብ መነሻ ሃሳብ
እንደምናደርገው ልባችንን መመርመር ከንቱ በሆነ እና በማይጠቅም ነገር ላይ ህይወታችንን ከማባከን ያድነናል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa